የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የዮሐንስ ወንጌል 4:4-26

የዮሐንስ ወንጌል 4:4-26 አማ54

በሰማርያም ሊያልፍ ግድ ሆነበት። ስለዚህ ያዕቆብ ለልጁ ለዮሴፍ በሰጠው ስፍራ አጠገብ ወደምትሆን ሲካር ወደምትባል የሰማርያ ከተማ መጣ፤ በዚያም የያዕቆብ ጕድጓድ ነበረ። ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ። ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች። ኢየሱስም፦ ውኃ አጠጪኝ አላት፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና። ስለዚህ ሳምራዊቲቱ፦ አንተ የይሁዳ ሰው ስትሆን ሳምራዊት ሴት ከምሆን ከእኔ መጠጥ እንዴት ትለምናለህ? አለችው፤ አይሁድ ከሳምራውያን ጋር አይተባበሩም ነበርና። ኢየሱስ መልሶ፦ የእግዚአብሔርን ስጦታና፦ ወኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት። ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ? በእውኑ አንተ ይህን ጕድጓድ ከሰጠን ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን? ራሱም ልጆቹም ከብቶቹም ከዚህ ጠጥተዋል አለችው። ኢየሱስም መልሶ፦ ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ሁሉ እንደ ገና ይጠማል፤ እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት። ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው። ኢየሱስም፦ ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ አላት። ሴቲቱ መልሳ፦ ባል የለኝም አለችው። ኢየሱስም፦ ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ፤ አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት። ሴቲቱ፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተ፦ ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው። ኢየሱስም እንዲህ አላት፦ አንቺ ሴት፥ እመኚኝ፥ በዚህ ተራራ ወይም በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ ይመጣል። እናንተስ ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ መዳን ከአይሁድ ነውና ለምናውቀው እንሰግዳለን። ነገር ግን በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል አሁንም ሆኖአል፤ አብ ሊሰግዱለት እንደ እነዚህ ያሉትን ይሻልና፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፥ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ያስፈልጋቸዋል። ሴቲቱ፦ ክርስቶስ የሚባል መሲሕ እንዲመጣ አውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ይነግረናል አለችው። ኢየሱስ፦ የምናገርሽ እኔ እርሱ ነኝ አላት።