የዮሐንስ ወንጌል 14
14
1“ልባችሁ አይታወክ፤ በእግዚአብሔር እመኑ፥ በእኔም ደግሞ እመኑ። 2በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ፤ እንዲህስ ባይሆን ባልኋችሁ ነበር፤ ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና 3ሄጄም ስፍራ ባዘጋጅላችሁ፥ እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ። 4ወደምሄድበትም ታውቃላችሁ፥ መንገዱንም ታውቃላችሁ።” 5ቶማስም፦ “ጌታ ሆይ፥ ወደምትሄድበት አናውቅም፤ እንዴትስ መንገዱን እናውቃለን?” አለው። 6ኢየሱስም፦ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም። 7እኔንስ ብታውቁኝ አባቴን ደግሞ ባወቃችሁ ነበር። አሁንም ጀምራችሁ ታውቁታላችሁ አይታችሁትማል” አለው።
8ፊልጶስ፦ “ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል” አለው። 9ኢየሱስም አለው፦ “አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦ ‘አብን አሳየን’ ትላለህ? 10እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነገራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል። 11እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።
12“እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥ 13እኔ ወደ አብ እሄዳለሁና አብም ስለ ወልድ እንዲከብር በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ። 14ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።
15-16“ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ በዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ 17እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።
18“ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም፤ ወደ እናንተ እመጣለሁ። 19ገና ጥቂት ዘመን አለ ከዚህም በኋላ ዓለም አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ እኔ ሕያው ነኝና እናንተ ደግሞ ሕያዋን ትሆናላችሁ። 20እኔ በአባቴ እንዳለሁ እናንተም በእኔ እንዳላችሁ እኔም በእናንተ እንዳለሁ በዚያን ቀን ታውቃላችሁ። 21ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትንም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” 22የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ፦ “ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው?” አለው። 23ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን። 24የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።
25ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤ 26አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል። 27ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም። 28እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር። 29ከሆነም በኋላ ታምኑ ዘንድ አሁን አስቀድሞ ሳይሆን። ነግሬአችኋለሁ። 30ከእእንግዲህ ወዲህ ከእናንተ ጋር ብዙ አልናገርም፥ የዚህ ዓለም ገዥ ይመጣልና፤ በእኔ ላይም አንዳች የለውም፤ 31ነገር ግን አብን እንድወድ ዓለም ሊያውቅ፥ አብም እንዳዘዘኝ፥ እንዲሁ አደርጋለሁ። ተነሡ፤ ከዚህ እንሂድ።
Currently Selected:
የዮሐንስ ወንጌል 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ