ከማርያምና ከእኅትዋ ከማርታ መንደር ከቢያትንያ የሆነ አልዓዛር የሚባል አንድ ሰው ታሞ ነበር። ማርያምም ጌታን ሽቱ የቀባችው እግሩንም በጠጕርዋ ያበሰሰችው ነበረች፤ ወንድምዋም አልዓዛር ታሞ ነበር። ስለዚህ እኅቶቹ “ጌታ ሆይ፥ እነሆ የምትወደው ታሞአል” ብለው ወደ እርሱ ላኩ። ኢየሱስም ሰምቶ፦ “ይህ ህመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም” አለ። ኢየሱስም ማርታንና እኅትዋን አልዓዛርንም ይወድ ነበር። እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤ ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ፦ “መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ኢየሱስም መልሶ፦ “ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤ በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል” አላቸው። ከዚህም በኋላ፦ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ፦ “ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል” አሉት። ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ፦ “አልዓዛር ሞተ፤ እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ” አላቸው። ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ” አለ። ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው። ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች። ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር። ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር። ማርታም ኢየሱስን፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ወንድምሽ ይነሣል” አላት።
የዮሐንስ ወንጌል 11 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 11:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos