ትንቢተ ኤርምያስ 52
52
1ሴዴቅያስ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሀያ አንድ ዓመት ጕልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም አሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፥ እናቱም አሚጣል የተባለች የሊብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 2ኢዮአቄምም እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 3ከፊቱም አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፥ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
4ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ በኢየሩሳሌም ላይ መጥተው ከበቡአት በዙሪያዋም ዕርድ አደረገ። 5ከተማይቱም እስከ ንጉሡ እስከ ሴዴቅያስ እስከ አሥራ አንደኛው ዓመት ድረስ ተከብባ ነበር። 6በአራተኛውም ወር በዘጠነኛው ቀን በከተማይቱ ራብ ጸንቶ ነበር፥ ለአገሩም ሰዎች እንጀራ ታጣ። 7ከተማይቱም ተሰበረች፥ ሰልፈኞችም ሁሉ ሸሹ፥ በሁለቱም ቅጥር መካከል ባለው በር ወደ ንጉሡ አትክልት በሚወስደው መንገድ በሌሊት ከከተማይቱ ወጡ። ከለዳውያንም በከተማይቱ ዙሪያ ነበሩ፥ በዓረባም መንገድ ሄዱ። 8የከለዳውያንም ሠራዊት ንጉሡን ተከታተሉት፥ በኢያሪኮም ሜዳ ሴዴቅያስን ያዙ፥ ሠራዊቱም ሁሉ ከእርሱ ዘንድ ተበትነው ነበር። 9ንጉሡንም ይዘው የባቢሎን ንጉሥ ወዳለባት በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ አመጡት፥ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 10የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በፊቱ ገደላቸው፥ የይሁዳንም አለቆች ሁሉ ደግሞ በሪብላ ገደላቸው። 11የሴዴቅያስንም ዓይኖች አወጣ፥ የባቢሎንም ንጉሥ በሰንሰለት አሰረው ወደ ባቢሎንም ወሰደው፥ እስኪሞትም ድረስ በግዞት ቤት አኖረው።
12በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር በአሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን በባቢሎን ንጉሥ ፊት የቆመው የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 13የእግዚአብሔርን ቤትና የንጉሡን ቤት አቃጠለ፥ የኢየሩሳሌምንም ቤቶች ሁሉ፥ ታላላቆችን ቤቶች ሁሉ፥ በእሳት አቃጠለ። 14ከዘበኞቹም አለቃ ጋር የነበረው የከለዳውያን ሠራዊት ሁሉ የኢየሩሳሌምን ቅጥር ሁሉ ዙሪያዋን አፈረሱ። 15የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን የሕዝቡን ድኆች፥ በከተማም ውስጥ የቀረውን ሕዝብ፥ ሸሽተውም ወደ ባቢሎን ንጉሥ የተጠጉትን፥ የሕዝቡንም ቅሬታ አፈለሰ። 16የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ከአገሩ ድኆች ወይን ተካዮችና አራሾች እንዲሆኑ አስቀረ።
17ከለዳውያንም በእግዚአብሔር ቤት የነበሩትን የናስ ዓምዶች በእግዚአብሔርም ቤት የነበሩትን መቀመጫዎችና የናሱን ኵሬ ሰባበሩ፥ ናሱንም ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 18ምንቸቶቹንና መጫሪያዎችንም መኰስተሪያዎችንና ድስቶችን ጭልፋዎችንም የሚያገለግሉበትንም የናስ ዕቃ ሁሉ ወሰዱ። 19የዘበኞቹም አለቃ ጽዋዎቹንና ማንደጃዎቹን ድስቶቹንና ምንቸቶችን መቅረዞችንና ጭልፋዎቹን መንቀሎችንም፥ የወርቁን ዕቃ በወርቅ፥ የብሩንም ዕቃ በብር አድርጎ፥ ወሰደ። 20ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት ያሠራቸውን ሁለቱን ዓምዶች፥ አንዱንም ኵሬ፥ ከመቀመጫዎቹም በታች የነበሩትን አሥራ ሁለቱን የናስ በሬዎች ወሰደ፥ ለእነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ናስ ሚዛን አልነበረም። 21ዓምዶቹም፥ የአንዱ ዓምድ ቁመት አሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፥ የዙሪያውም መጠን አሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፥ ውፍረቱም አራት ጣት ያህል ነበረ፥ ባዶም ነበረ። 22የናሱም ጕልላት በላዩ ነበረ፥ የአንዱም ጉልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ፥ በጕልላቱም ላይ በዙሪያው ሁሉ ከናስ የተሠሩ መረበብና ሮማኖች ነበሩበት፥ በሁለተኛውም ዓምድ ደግሞ እንደዚህ ያለ ነገርና ሮማኖች ነበሩበት። 23በስተ ውጭም ዘጠና ስድስት ሮማኖች ነበሩ። በመረበቡም ዙሪያ የነበሩ ሮማኖች ሁሉ አንድ መቶ ነበሩ።
24የዘበኞቹም አለቃ ታላቁን ካህን ሠራያን ሁለተኛውንም ካህን ሶፎንያስን ሦስቱንም በረኞች ወሰደ፥ 25ከከተማይቱም በሰልፈኞች ላይ ተሾመው ከነበሩት አንዱን ጃንደረባ፥ በከተማይቱም ከሚገኙት በንጉሡ ፊት ከሚቆሙት ሰባቱን ሰዎች፥ የአገሩንም ሕዝብ የሚያሰልፈውን የሠራዊቱን አለቃ ጸሐፊ፥ በከተማይቱም ከተገኙት ከአገሩ ሕዝብ ስድሳ ሰዎች ወሰደ። 26የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ወስዶ የባቢሎን ንጉሥ ወዳለበት ወደ ሪብላ አመጣቸው። 27የባቢሎንም ንጉሥ መታቸው፥ በሐማትም ምድር ባለችው በሪብላ ገደላቸው። እንዲሁ ይሁዳ ከአገሩ ተማረከ።
28ናቡከደነፆር የማረከው ሕዝብ ይህ ነው፥ በሰባተኛው ዓመት ሦስት ሺህ ሀያ ሦስት አይሁድ፥ 29ናቡከደነፆርም በአሥራ ስምንተኛው ዓመት ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ነፍስ ከኢየሩሳሌም ማርኮአል፥ 30በናቡከደነፆር በሀያ ሦስተኛው ዓመት የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን ከአይሁድ ሰባት መቶ አርባ አምስት ነፍስ ማርኮአል፥ ሰዎች ሁሉ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ።
31እንዲህም ሆነ፥ የይሁዳ ንጉሥ ዮአኪን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በአሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሀያ አምስተኛው ቀን፥ የባቢሎን ንጉሥ ዮርማሮዴክ በነገሠ በአንደኛው ዓመት የይሁዳን ንጉሥ የዮአኪንን ራስ ከፍ ከፍ አደረገ ከወህኒም አወጣው፥ 32በመልካምም ተናገረው፥ ዙፋኑንም ከእርሱ ጋር በባቢሎን ከነበሩት ነገሥታት ዙፋን በላይ አደረገለት። 33በወህኒም ውስጥ ለብሶት የነበረውን ልብስ ለወጠለት፥ ዮአኪንም በሕይወቱ ዘመን ሁሉ በፊቴ ሁልጊዜ እንጀራ ይበላ ነበር። 34የባቢሎንም ንጉሥ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እስኪሞት ድረስ የዘወትር ቀለብ ዕለት ዕለት ይሰጠው ነበር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 52: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ