የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 46

46
1ስለ አሕዛብ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2ስለ ግብጽ፥ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርከሚሽ ስለ ነበረው፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ መታው ስለ ግብጽ ንጉሥ ስለ ፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት።
3ጋሻ ጦር አዘጋጁ ወደ ሰልፍም ቅረቡ። 4ፈረሰኞች ሆይ፥ ፈረሶችን ለጕሙና ውጡ፥ ራስ ቍርንም ደፍታችሁ ቁሙ፥ ጦርንም ሰንግሉ ጥሩርንም ልበሱ። 5ፈርተው ወደ ኋላ ሲመለሱ፥ ኃያላኖቻቸውም ሲደበደቡ ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሲሸሹ ለምን አየሁ? በዚህና በዚያ ድንጋጤ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር። 6ፈጣኑ አያመልጥም ኃያሉም አይድንም፥ በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል ተሰናክለው ወደቁ። 7ይህ እንደ ግብጽ ወንዝ የሚነሣ፥ ውኃውም እንደ ወንዝ የሚናወጥ ማን ነው? 8ግብጽ እንደ ግብጽ ወንዝ ይነሳል ውኃውም እንደ ወንዙ ይናወጣል፥ እርሱም፦ እነሣለሁ ምድርንም ሁሉ እከድናለሁ፥ ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ ብሎአል። 9ፈረሶች ሆይ፥ ውጡ፥ ሰረገሎችም ሆይ፥ ንጐዱ፥ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የፉጥ ኃያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኃያላን ይውጡ። 10ያ ቀን ጠላቶቹን የሚበቀልበት የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፥ ሰይፍ በልቶ ይጠግባል በደማቸውም ይሰክራል፥ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ መሥዋዕት አለውና። 11ድንግሊቱ የግብጽ ልጅ ሆይ፥ ወደ ገለዓድ ውጪ የሚቀባንም መድኃኒት ውሰጂ፥ መድኃኒትን ያበዛሽው በከንቱ ነው፥ መዳን የለሽም። 12ኃያሉ በኃያሉ ላይ ተሰናክሎ ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ ጕስቍልናሽን ሰምተዋል፥ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል።
13የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንዲመጣና የግብጽን ምድር እንዲመታ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
14በግብጽ ተናገሩ፥ በሚግዶልም አሰሙ፥ በሜምፎስና በጣፍናስ አሰሙ፥ ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና፦ ተነሥ ተዘጋጅም በሉ። 15ኃይለኞችህ ስለ ምን ተወገዱ? እግዚአብሔር ስላደከማቸው አልቆሙም። 16ብዛታቸውም ተሰናከለ፥ ሰውም አንዱ በአንዱ ላይ ወደቀ፥ እነርሱም፦ ተነሡ፥ ከሚያስጨንቅ ሰይፍ ፊት ወደ ወገናችን ወደ ተወለድንባት ምድር እንመለስ አሉ። 17በዚያም የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን፦ ሰዓቱን የሚያሳልፍ ጕረኛ ብለው ጠሩት። 18እኔ ሕያው ነኝና በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ ታቦር፥ በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የተባለው ንጉሥ። 19አንቺ በግብጽ የምትቀመጪ ልጅ ሆይ፥ ሜምፎስ ባድማ ትሆናለችና፥ ትቃጠልማለችና፥ የሚቀመጥባትም አይገኝምና ለምርኮ የሚሆን ዕቃ አዘጋጂ። 20ግብጽ የተዋበች ጊደር ናት፥ ጥፋት ግን ይመጣል፥ ከሰሜን በኩል ይመጣባታል። 21በእርስዋም ያሉ የተቀጠሩ ሠራተኞች እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፥ የጥፋታቸው ቀንና የመጐብኘታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፥ በአንድነትም ሸሹ፥ አልቆሙምም። 22ከሠራዊትም ጋር ይሄዳሉና ድምፅ እንደ እባብ ይተምማል፥ እንደ እንጨት ቈራጮችም በምሳር ይመጡባታል። 23ይቈጠሩ ዘንድ የማይቻሉትን የዱርዋን ዛፎች ይቈርጣሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ከአንበጣ ይልቅ በዝተዋልና ቍጥርም የላቸውምና። 24የግብጽ ልጅ ታፍራለች፥ በሰሜን ሕዝብ እጅ አልፋ ትሰጣለች። 25የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ፥ 26ነፍሳቸውንም በሚፈልጉ ሰዎች እጅ፥ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በባሪያዎቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፥ ይላል እግዚአብሔር።
27ነገር ግን አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ አትፍራ፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ አትደንግጥ፥ እነሆ፥ አንተን ከሩቅ ዘርህንም ከተማረከባት ምድር አድናለሁ፥ ያዕቆብም ተመልሶ ያርፋል ተዘልሎም ይቀመጣል፥ ማንም አያስፈራውምም። 28አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ አንተንም ያሰደድሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፥ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም አልተውህም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ