ትንቢተ ኤርምያስ 41
41
1በሰባተኛውም ወር ከመንግሥት ወገንና ከንጉሡ ዋና ዋና አለቆች አንዱ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከአሥር ሰዎች ጋር ወደ ምጽጳ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፥ በዚያም በምጽጳ በአንድ ላይ እንጀራ በሉ። 2የናታንያም ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩት አሥሩ ሰዎች ተነሥተው የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱ፥ የባቢሎንም ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን ገደሉ። 3እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር በምጽጳ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፥ በዚያም የተገኙትን የከለዳውያንን ሰልፈኞች ሁሉ ገደላቸው።
4ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ ማንም ሳያውቅ በሁለተኛው ቀን 5ጢማቸውን ላጭተው ልብሳቸውንም ቀድደው ገላቸውንም ነጭተው፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት ያቀርቡ ዘንድ የእህል ቍርባንና ዕጣን በእጃቸው እየያዙ፥ ሰማንያ ሰዎች ከሴኬምና ከሴሎ ከሰማርያም መጡ። 6የናታንያም ልጅ እስማኤል ከምጽጳ ወጥቶ እያለቀሰ ሊገናኛቸው ሄደ፥ በተገናኛቸውም ጊዜ፦ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ አላቸው። 7ወደ ከተማም መካከል በመጡ ጊዜ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ገደሉአቸው፥ በጕድጓድም መካከል ጣሉአቸው። 8በመካከላቸውም እስማኤልን፦ በሜዳ የተሸሸገ ስንዴና ገብስ ዘይትና ማርም አለንና አትግደለን የሚሉት አሥር ሰዎች ተገኙ። እርሱም ተዋቸው፥ ከወንድሞቻቸውም ጋር አልገደላቸውም። 9እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር የገደላቸውን የሰዎች ሬሳ ሁሉ የጣለበት ጕድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ የሠራው ጕድጓድ ነበረ፥ የናታንያም ልጅ እስማኤል የገደላቸውን ሞላበት። 10እስማኤልም በምጽጳ የነበረውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ የንጉሡን ሴቶች ልጆች የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ የሰጠውን በምጽጳ የቀሩትን ሕዝብ ሁሉ ማረካቸው፥ የናታንያም ልጅ እስማኤል ማርኮ ወደ አሞን ልጆች ይሄድ ዘንድ ተነሣ።
11የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ከእርሱም ጋር የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል ያደረገውን ክፋት ሁሉ በሰሙ ጊዜ፥ 12ሰዎቹን ሁሉ ይዘው ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ጋር ሊዋጉ ሄዱ፥ በገባዖንም ባለው በታላቁ ውኃ አጠገብ አገኙት። 13ከእስማኤልም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የቃሬያን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆችን ሁሉ ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14እስማኤልም ከምጽጳ የማረካቸው ሕዝብ ሁሉ ዘወር ብለው ተመለሱ፥ ወደ ቃሬያም ልጅ ወደ ዮሐናን ሄዱ። 15የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን ከስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ ወደ አሞንም ልጆች ሄደ።
16የቃሬያም ልጅ ዮሐናን ከእርሱም ጋር የነበሩት የጭፍራ አለቆች ሁሉ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በምጽጳ ከገደለው በኋላ ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ያስመለሱአቸውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ ከገባዖን ያስመለሱአቸውን ሰልፈኞች፥ ሴቶችንም፥ ልጆችንም፥ ጃንደረቦችንም፥ ወሰዱ፥ 17ተነሥተውም ወደ ግብጽ ይሄዱ ዘንድ በቤተልሔም አጠገብ ባለው በጌሮት ከመዓም ተቀመጡ፥ 18እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ በአገሩ ላይ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ስለ ገደለው ከለዳውያንን ፈርተዋልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 41: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ