ትንቢተ ኤርምያስ 39

39
1ኢየሩሳሌምም በተያዘች ጊዜ፥ በይሁዳ ንጉሥ በሴዴቅያስ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፥ 2በሴዴቅያስም በአሥራ አንደኛው ዓመት በአራተኛው ወር ከወሩም በዘጠነኛው ቀን ከተማይቱ ተሰበረች። 3የባቢሎንም ንጉሥ አለቆች ሁሉ፥ ኤርጌል ሳራስር፥ ሳምጋርናቦ፥ ሠርሰኪም፥ ራፌስ፥ ኤርጌል ሳራስር፥ ራብማግ፥ ከቀሩት ከባቢሎን ንጉሥ አለቆች ሁሉ ጋር ገብተው በመካከለኛው በር ውስጥ ተቀመጡ።
4የይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ ሰልፈኞቹም ሁሉ ባዩአቸው ጊዜ ኰበለሉ፥ በሌሊትም በንጉሡ አትክልት መንገድ በሁለቱ ቅጥር መካከል ከነበረው ደጅ ከከተማይቱ ወጡ፥ በዓረባም መንገድ ወጡ። 5የከለዳውያንም ሠራዊት ተከታተላቸው፥ ሴዴቅያስንም በኢያሪኮ ሜዳ አገኙት፥ ይዘውም በሐማት ምድር ወዳለችው ወደ ሪብላ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወደ ናቡከደነፆር አመጡት፥ እርሱም ፍርድን በእርሱ ላይ ተናገረ። 6የባቢሎንም ንጉሥ የሴዴቅያስን ልጆች በዓይኑ ፊት በሪብላ ገደላቸው፥ የባቢሎንም ንጉሥ የይሁዳን ከበርቴዎች ሁሉ ገደለ። 7የሴዴቅያስንም ዓይን አወጣ፥ ወደ ባቢሎንም ይወስደው ዘንድ በሰንሰለት አሰረው። 8ከለዳውያንም የንጉሡንና የሕዝቡን ቤቶች በእሳት አቃጠሉ፥ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር አፈረሱ። 9የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን በከተማይቱ የቀሩትን ሕዝብ ወደ እርሱም የኰበለሉትን ሰዎች የቀረውንም የሕዝቡን ቅሬታ ወደ ባቢሎን ማረካቸው። 10አንዳች ከሌላቸው ከሕዝቡ ድሆች ግን የዘበኞቹ አለቃ ናቡዘረዳን በይሁዳ አገር ተዋቸው፥ የወይኑን ቦታና እርሻውን በዚያን ጊዜ ሰጣቸው።
11-12የባቢሎንም ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ ኤርምያስ፦ ውሰደውና በመልካም ተመልከተው፥ የሚሻውንም ነገር አድርግለት እንጂ ክፉን ነገር አታድርግበት ብሎ የዘበኞቹን አለቃ ናቡዘረዳንን አዘዘ። 13የዘበኞቹም አለቃ ናቡዘረዳን ላከ፥ ናቡሽዝባንም ራፋስቂስም ኤርጌል ሳራስርም ራብማግም የባቢሎንም ንጉሥ ዋና ዋና አለቆች ሁሉ ላኩ፥ 14ኤርምያስንም ከግዞት ቤት አደባባይ አወጡት፥ ወደ ቤቱም ይወስደው ዘንድ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፥ እንዲህም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ።
15በግዞትም ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ፦ 16ሂድ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፦ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፥ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። 17በዚያ ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም። 18ፈጽሜ አድንሃለሁ ነፍስህም እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፥ በእኔ ታምነሃልና፥ ይላል እግዚአብሔር።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ