የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኤርምያስ 12

12
1አቤቱ፥ ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፥ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኃጢአተኞች መንገድ ስለምን ይቃናል? በደልንስ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለምን ደኅንነት ይሆናል? 2ተክለሃቸዋል፥ ሥር ሰድደዋል፥ አድገዋል አፍርተውማል፥ በአፋቸው አንተ ቅርብ ነህ፥ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ። 3አንተ ግን፥ አቤቱ፥ አውቀኸኛል፥ አይተኸኛል፥ ልቤንም በፊትህ ፈትነሃል፥ እንደ በጎች ለመታረድ ጐትተህ ለያቸው፥ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው። 4ምድሪቱ የምታለቅሰው፥ የአገሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቸ ነው? የተቀመጡባት ሰዎች፦ ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና ስለ ክፋታቸው እንስሶችና ወፎች ጠፍተዋል።
5ከእግረኞች ጋር በሮጥህ ጊዜ እነርሱ ቢያደክሙህ፥ ከፈረሶች ጋር መታገል እንዴት ትችላለህ? በሰላምም ምድር ታምነህ ብትቀመጥ፥ በዮርዳኖስ ትዕቢት እንዴት ታደርጋለህ? 6ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር አታልለውሃልና፥ በኋላህም ጮኸዋልና፥ በመልካምም ቢናገሩህም አትታመናቸው።
7ቤቴን ትቼአለሁ ርስቴንም ጥያለሁ፥ ነፍሴም የምትወድዳትን በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ። 8ርስቴ በዱር እንዳለ አንበሳ ሆናብኛለች፥ ድምፅዋን አንሥታብኛለች፥ ስለዚህ ጠልቻታለሁ። 9ርስቴ እንደ ዝንጕርጕር አሞራ ሆነችብኝን? አሞሮችስ በዙሪያዋና በላይዋ ሆነዋልን? ሂዱ፥ የምድር አራዊትን ሁሉ ሰብስቡ፥ ይበሉም ዘንድ አምጡአቸው። 10ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፥ እድል ፈንታዬንም ረግጠዋል፥ የአምሮቴን እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገውታል። 11ባድማ አድርገውታል፥ ፈርሶም ወደ እኔ ያለቅሳል፥ ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች በልቡም የሚያስባት የለም። 12በወናዎች ኮረብቶች ሁሉ ላይ በዝባዦች መጥተዋል፥ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፥ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም። 13ስንዴን ዘሩ እሾህንም አጨዱ፥ ደከሙ፥ ምንም አልረባቸውም፥ ስለ እግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ ከፍሬያችሁ ታፍራላችሁ።
14እግዚአብሔር ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጐረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና፦ እነሆ፥ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፥ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ። 15ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ እምራቸዋለሁ፥ እያንዳንዱንም ወደ ርስቱ እያንዳንዱንም ወደ ምድሩ እመልሳለሁ። 16በበኣል ይምሉ ዘንድ ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ብለው ይምሉ ዘንድ የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩ፥ በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ። 17ባይሰሙኝ ግን ያንን ሕዝብ ፈጽሜ እነቅለዋለሁ አጠፋውማለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ