ትንቢተ ኢሳይያስ 59
59
1እነሆ፥ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፥ ጆሮውም ከመስማት አልደነቈረችም፥ 2ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። 3እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፥ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል። 4በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም፥ በምናምንቴ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል፥ ጕዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል። 5የእባብን እንቍላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ፥ እንቍላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቍላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል። 6ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ በሥራቸውም አይሸፈኑም፥ ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው። 7እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ፥ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ። 8የሰላምን መንገድ አያውቁም፥ በአካሄዳቸውም ፍርድ የለም፥ መንገዳቸውን አጣምመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም። 9ስለዚህ ፍርድ ከእኛ ዘንድ ርቆአል፥ ጽድቅም አላገኘንም፥ ብርሃንን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ እነሆም፥ ጨለማ ሆነ፥ ጸዳልን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር፥ ነገር ግን በጨለማ ሄድን። 10እንደ ዕውሮች ወደ ቅጥሩ ተርመሰመስን፥ ዓይን እንደ ሌላቸው ተርመሰመስን፥ በቀትር ጊዜ በድግዝግዝታ እንዳለ ሰው ተሰናከልን፥ እንደ ሙታን በጨለማ ስፍራ ነን። 11ሁላችን እንደ ድቦች እንጮኻለን፥ እንደ ርግብ እንለቃቀሳለን፥ ፍርድን በተስፋ እንጠባበቅ ነበር እርሱም የለም፥ መዳንም ከእኛ ዘንድ ርቆአል። 12ዓመፃችን በአንተ ፊት በዝቶአልና፥ ኃጢአታችን መስክሮብናልና፥ ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፥ በደላችንን እናውቃለንና። 13ዐምፀናል፥ ሐሰትን ተንግረናል፥ አምላካችንንም ከመከተል ተመልሰናል፥ ግፍንና ዓመፅንም ተናግረናል፥ የኃጢአት ቃልንም ፀንሰን ከልብ አውጥተናል። 14ፍርድም ወደ ኋላ ተመልሶአል፥ ጽድቅም በሩቅ ቆሞአል፥ እውነትም በአደባባይ ላይ ወድቆአልና፥ ቅንነትም ሊገባ አልቻለምና። 15እውነትም ታጥቶአል፥ ከክፋትም የራቀ ሰው ለብዝበዛ ሆኖአል። እግዚአብሔርም አየ፥ ፍርድም ስለሌለ ተከፋ። 16ሰውም እንደ ሌለ አየ፥ ወደ እርሱ የሚማልድ እንደ ሌለ ተረዳ ተደነቀም፥ ሰለዚህ የገዛ ክንዱ መድኃኒት አመጣለት፥ ጽድቁም አገዘው። 17ጽድቅንም እንደ ጥሩር ለበሰ፥ በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፥ የበቀልንም ልብስ ለበሰ፥ በቅንዓትም መጐናጸፊያ ተጐናጸፈ። 18እንደ ሥራቸው መጠን እንዲሁ ቍጣን ለባላጋራዎቹ፥ ፍዳንም ለጠላቶቹ ይከፍላል፥ ለደሴቶችም ፍዳቸውን ይከፍላል። 19እርሱ የእግዚአብሔር ነፋስ እንደሚነዳው እንደ ጐርፍ ፈሳሽ ይመጣልና በምዕራብ ያሉት የእግዚአብሔርን ስም፥ በፀሐይ መውጫም ያሉት ክብሩን ይፈራሉ። 20ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 21ከእነርሱ ጋር ያለው ቃል ኪዳኔ ይህ ነው ይላል እግዚአብሔር፥ በአንተ ላይ ያለው መንፈሴ በአፍህም ውስጥ ያደረግሁት ቃሌ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም ድረስ ከአፍህ ከዘርህም አፍ ከዘር ዘርህም አፍ አያልፍም፥ ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 59: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ