ትንቢተ ኢሳይያስ 52
52
1ጽዮን ሆይ፥ ተነሺ፥ ተነሺ፥ ኃይልሽን ልበሺ፥ ቅድስቲቱ ከተማ ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ያልተገረዘና ርኩስ ከእንግዲህ ወዲህ አይገባብሽምና ጌጠኛ ልብስሽን ልበሺ። 2ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ትቢያን አራግፊ፥ ተነሺ፥ ተቀመጪ፥ ምርኮኛይቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ የአንገትሽን እስራት ፍቺ። 3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በከንቱ ተሽጣችሁ ነበር፥ ያለ ገንዘብም ትቤዣላችሁ። 4ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወገኔ በዚያ እንግዳ ሆኖ ይቀመጥ ዘንድ አስቀድሞ ወደ ግብጽ ወረደ፥ አሦርም ያለ ምክንያት በደለው። 5ወገኔ በከንቱ ተወስዶአልና አሁን ከዚህ ምን አለኝ? ይላል እግዚአብሔር፥ የሚገዙአቸው ይጮኻሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ስሜም ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ይሰደባል። 6ስለዚህ ወገኔ ስሜን ያውቃል፥ ስለዚህም የምናገር እኔ እንደ ሆንሁ በዚያ ቀን ያውቃሉ፥ እነሆ፥ እኔ ነኝ። 7የምስራች የሚናገር፥ ሰላምንም የሚያወራ፥ የመልካምንም ወሬ የምስራች የሚናገር፥ መድኃኒትንም የሚያወራ፥ ጽዮንንም፦ አምላክሽ ነግሦአል የሚል ሰው እግሩ በተራሮች ላይ እጅግ ያማረ ነው። 8እነሆ፥ ጕበኞችሽ ጮኸዋል፥ እግዚአብሔር ወደ ጽዮን በተመለሰ ጊዜ ዓይን በዓይን ይተያያሉና ድምፃቸውን ያነሣሉ፥ በአንድነትም ይዘምራሉ። 9እናንተ የኢየሩሳሌም ፍርስራሾች ሆይ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን አጽናንቶአልና፥ ኢየሩሳሌምንም ታድጎአልና ደስ ይበላችሁ፥ በአንድነትም ዘምሩ። 10እግዚአብሔር የተቀደሰውን ክንዱን በአሕዛብ ሁሉ ፊት ገልጦአል፥ በምድር ዳርቻ የሚኖሩትም ሁሉ የአምላካችንን መድኃኒት ያያሉ። 11እናንተ የእግዚአብሔር ዕቃ የምትሸከሙ ሆይ፥ እልፍ በሉ፥ እልፍ በሉ፥ ከዚያ ውጡ፥ ርኩስን ነገር አትንኩ፥ ከመካከልዋ ውጡ፥ ንጹሐን ሁኑ። 12እግዚአብሔር ይቀድማችኋልና፥ የእስራኤልም አምላክ ይከተላችኋልና በችኮላ አትወጡም በመኮብለልም አትሄዱም። 13እነሆ፥ ባሪያዬ በማስተዋል ያደርጋል፥ ይከብራል ከፍ ከፍም ይላል፥ እጅግ ታላቅም ይሆናል። 14ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፥ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቍሎአልና ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፥ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፥ 15ያልተነገረላቸውን ያያሉና፥ ያልሰሙትንም ያስተውላሉና ነገሥታት ስለ እርሱ አፋቸውን ይዘጋሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 52: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ