የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 50

50
1እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናታችሁን የፈታሁበት የፍቺዋ ጽሕፈት የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥሁ ከአበዳሪዎች ለየትኛው ነው? እነሆ፥ ስለ ኃጢአታችሁ ተሸጣችኋል፥ ስለ በደላችሁም እናታችሁ ተፈትታለች። 2በመጣሁስ ጊዜ ሰው ስለ ምን አልነበረም? በጠራሁስ ጊዜ የሚመልስ ስለ ምን አልነበረም? መታደግ እንዳትችል እጄ አጭር ሆናለችን? ወይስ ለማዳን ኃይል የለኝምን? እነሆ፥ በገሠጽሁ ጊዜ ባሕርን አደርቃለሁ፥ ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋቸዋለሁ፥ ውኃም በማጣት ዓሦቻቸው ይገማሉ በጥማትም ይሞታሉ። 3ሰማያትን ጥቍረት አለብሳቸዋለሁ፥ መጋረጃቸውንም ማቅ አደርጋለሁ። 4የደከመውን በቃል እንዴት እንደምደግፍ አውቅ ዘንድ ጌታ እግዚአብሔር የተማሩትን ምላስ ሰጥቶኛል፥ ማለዳ ማለዳ ያነቃኛል፥ እንደ ተማሪዎችም ትሰማ ዘንድ ጆሮዬን ያነቃቃል። 5ጌታ እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶአል፥ እኔም ዓመፀኛ አልነበርሁም ወደ ኋላዬም አልተመለስሁም። 6ጀርባዬን ለገራፊዎች ጕንጬንም ለጠጕር ነጪዎች ሰጠሁ፥ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም። 7ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛልና ስለዚህ አልታወክሁም፥ ስለዚህም ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌዋለሁ፥ እንዳላፍርም አውቃለሁ። 8የሚያጸድቀኝ ቅርብ ነው፥ ከእኔስ ጋር የሚከራከር ማን ነው? በአንድነት እንቁም፥ የሚከራከረኝ ማን ነው? ወደ እኔ ይቅረብ። 9እነሆ፥ ጌታ እግዚአብሔር ይረዳኛል፥ ማን ይፈርድብኛል? እነሆ፥ ሁሉ እንደ ልብስ ያረጃሉ ብልም ይበላቸዋል። 10ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ፥ በጨለማም የሚሄድ፥ ብርሃንም የሌለው፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም የሚታመን፥ በአምላኩም የሚደገፍ ማን ነው? 11እነሆ፥ እሳት የምታነድዱ የእሳትንም ወላፈን የምትታጠቁ ሁላችሁ፥ በእሳታችሁ ነበልባል ባነደዳችሁትም ወላፈን ሂዱ፥ ይህ ከእጄ ይሆንባችኋል፥ በኅዘን ትተኛላችሁ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ