ትንቢተ ኢሳይያስ 43
43
1አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፥ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። 2በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፥ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም። 3እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፥ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። 4በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። 5እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። 6-7ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም፦ አትከልክል፥ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። 8ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮዎችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ። 9አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ ወገኖችም ይከማቹ፥ ከመካከላቸው ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም፦ እውነት ነው ይበሉ። 10ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፥ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። 11እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። 12ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፥ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ። 13ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፥ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው? 14የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከላዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። 15ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። 16እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፥ 17እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፥ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፥ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 18የፊተኛውን ነገር አታስታውሉ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። 19እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፥ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሃም ወንዞችን አደርጋለሁ። 20-21ምሥጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፥ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል። 22ያዕቆብ ሆይ፥ አንተ ግን አልጠራኸኝም፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ደክመሃል። 23ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፥ በእህልም ቍርባን አላስቸገርሁህም በዕጣንም አላደከምሁህም። 24ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፥ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርኸኝ፥ በበደልህም አደከምኸኝ። 25መተላለፍህን፦ ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፥ ኃጢአትህንም አላስብም። 26አሳስበኝ፥ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፥ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር። 27ፊተኛው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፥ መምህሮችህም በድለውኛል። 28ስለዚህ የመቅደሱን አለቆች አረከስሁ፥ ያዕቆብንም እርግማን፥ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 43: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ