ትንቢተ ኢሳይያስ 3
3
1እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፥ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውሃውንም ድጋፍ ሁሉ፥ 2ኃያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነብዩንም፥ ምዋርተኛውንም፥ ሽማግሌውንም፥ 3የአምሳ አለቃውንም፥ ከበርቴውን፥ አማካሪውንም፥ ብልሁንም ሠራተኛ፥ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል። 4አለቆቻቸው እንዲሆኑ ብላቴኖችን አስነሣባቸዋለሁ፥ ሕፃናቶችም ይገዙአቸዋል። 5ሕዝቡም፥ ሰው በሰው ላይ ሰውም በባልንጀራው ላይ፥ ይገፋፋል፥ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኮራል። 6ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ፦ አንተ ልብስ አለህ አለቃም ሁንልን ይህችም ባድማ ከእጅህ በታች ትሁን ሲለው፥ 7በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፦ እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም፥ በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም ይላል። 8የክብሩን ዓይን ያስቈጡ ዘንድ ምላሳቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ። 9የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፥ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፥ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ክፉ ነገርን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ! 10የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን፦ መልካም ይሆንልሃል በሉት። 11እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል። 12ሕዝቤንስ አስገባሪዎቻቸው ይገፍፉአቸዋል፥ አስጨናቂዎችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ። 13እግዚአብሔር ለፍርድ ተነሥቶአል በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል። 14እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፥ የወይኑን ቦታ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ፥ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፥ 15ሕዝቤንም ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 16ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ የጽዮን ቈነጃጅት ኮርተዋልና፥ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፥ ፈንጠርም እያሉ፥ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉና 17ስለዚህ ጌታ የጽዮንን ቆነጃጅት አናት በቡሀነት ይመታል፥ እግዚአብሔርም ኀፍረተ ሥጋችውን ይገልጣል። 18በዚያም ቀን ጌታ የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበብንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ 19የጆሮ እንጥልጥሉንም፥ አንባሩንም፥ 20መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥ ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥ አሸንክታቡንም፥ 21የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥ የዓመት በዓልንም ልብስ፥ 22መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥ መስተዋቱንም፥ 23ከጥሩ በፍታ የተሠራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል። 24እንዲህም ይሆናል፥ በሽቱ ፋንታ ግማት፥ በመታጠቂያውም ፋንታ ገመድ፥ ጠጕርንም በመንቀስ ፋንታ ቡሀነት፥ በመጎናጸፊያ ፋንታ ማቅ፥ በውበትም ፋንታ ጠባሳ ይሆናል። 25ጕልማሶችሽ በሰይፍ፥ ኃያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ። 26በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፥ እርስዋም ብቻዋን በምድር ላይ ትቀመጣለች።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 3: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ