ትንቢተ ኢሳይያስ 21
21
1በባሕር አጠገብ ስላለው ስለ ምድረ በዳ የተነገረ ሸክም። ዐውሎ ነፋስ ከደቡብ እንደሚወጣ፥ እንዲሁ ከሚያስፈራ አገር ከምድረ በዳ ይወጣል። 2ከባድ ራእይ ተነገረኝ፥ ወንጀለኛው ይወነጅላል አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፥ ውጪ! ሜዶን ሆይ፥ ክበቢ፥ ትካዜውን ሁሉ አስቀርቻለሁ። 3ስለዚህ ወገቤ ሕመም ተሞላ፥ እንደምትወልድ ሴት ምጥ ያዘኝ፥ ከሕመሜ የተነሣ አልሰማም፥ ከድንጋጤም የተነሣ አላይም። 4ልቤ ተንበደበደ፥ ድንጋጤ አስፈራኝ፥ ተስፋ ያደረግሁትም ድንግዝግዝታ መንቀጥቀጥ ሆነብኝ። 5ማዕዱን ያዘጋጃሉ፥ ምንጣፉንም ይዘረጋሉ፥ ይበሉማል፥ ይጠጡማል፥ እናንተ መሳፍንት ሆይ፥ ተነሡ፥ ጋሻውን አዘጋጁ። 6ጌታ እንዲህ ብሎኛልና፦ ሂድ ጕበኛም አቁም፥ የሚያየውንም ይናገር። 7በከብት የሚቀመጡትን፥ ሁለት ሁለት እየሆኑ የሚሄዱት ፈረሰኞች፥ በአህዮች የሚቀመጡትንና በግመሎች የሚቀመጡትን ባየ ጊዜ በጽኑ ትጋት አስተውሎ ተግቶም ያድምጥ። 8ያየውም፦ ጌታ ሆይ፥ ቀኑን ሁሉ ዘወትር በማማ ላይ ቆሜአለሁ፥ ሌሊቱንም ሁሉ በመጠበቂያዬ ላይ ተተክያለሁ፥ 9እነሆም፥ በፈረሶች የሚቀመጡ፥ ሁለት ሁለት ሁነው የሚሄዱ ፈረሰኞች ይመጣሉ ብሎ ጮኸ፥ እርሱም መልሶ፦ ባቢሎን ወደቀች ወደቀች፥ የተቀረጹም የአማልክቶችዋ ምስሎች ሁሉ በምድር ላይ ተጥለው ደቀቁ አለ። 10እናንተ በአውድማዬ ላይ የተወቃችሁ የአውድማዬ ልጆች ሆይ፥ ከእስራኤል አምላክ ከሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሰማሁትን ነገርኋችሁ። 11ስለ ኤዶሚያስ የተነገረ ሸክም። አንዱ ከሴይር፦ ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ጕበኛ ሆይ፥ ሌሊቱ ምን ያህል ነው? ብሎ ጠራኝ። 12ጕበኛውም፦ ይነጋል ደግሞም ይመሻል፥ ትጠይቁ ዘንድ ብትወድዱ ጠይቁ፥ ተመልሳችሁም ኑ አለ። 13ስለ ዓረብ የተነገረ ሸክም። የድዳናውያን ነጋዴዎች ሆይ፥ በዓረብ ዱር ወስጥ ታድራላችሁ። 14በቴማም የሚትኖሩ ሆይ፥ ወደ ተጠሙት ሰዎች ውኃ አምጡ፥ እንጀራ ይዛችሁ የሸሹትን ሰዎች ተቀበሉአቸው። 15ከሰይፍ፥ ከተመዘዘው ሰይፍ፥ ከተለጠጠውም ቀስት ከጽኑም ሰልፍ ሸሽተዋልና። 16ጌታ እንዲህ ብሎኛልና፦ እንደ ምንደኛ ዓመት በአንድ ዓመት ውስጥ የቄዳር ክብር ሁሉ ይጠፋል፥ 17ከቀስተኞች ቍጥር የቀሩት፥ የቄዳር ልጆች ኃያላን፥ ያንሳሉ፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 21: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ