ትንቢተ ኢሳይያስ 17
17
1ስለ ደማስቆ የተነገረ ሸክም። እነሆ፥ ደማስቆ ከተማ ከመሆን ተቋርጣለች፥ ባድማና የፍርስራሽ ክምር ትሆናለች። 2ከተሞችዋ ለዘላለም የተፈቱ ይሆናሉ፥ ለመንጋ ማሰማርያ ይሆናሉ፥ መንጎች በዚያ ያርፋሉ የሚያስፈራቸውም የለም። 3ምሽግም ከኤፍሬም፥ መንግሥትም ከደማስቆ ተወገደች የሶርያም ቅሬታ እንደ እስራኤል ልጆች ክብር ይሆናል ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 4በዚያን ቀን እንዲህ ይሆናል፥ የያዕቆብ ክብር ይደክማል የሥጋውም ውፍረት ይከሳል። 5አጫጅ የቆመውን እህል በእጁ ሰብስቦ ዛላውን እንደሚያጭድ ይሆናል፥ በራፋይም ሸለቆ ቃርሚያ እንደሚለቅም ይሆናል። 6ወይራ በተመታ ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ፍሬ በራሱ ላይ እንደሚቀር፥ አራት ወይም አምስት በዛፊቱ ጫፍ እንደሚገኝ፥ በእርሱ ዘንድ ቃርሚያ ይቀራል ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር። 7በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፥ ዓይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ። 8እጁም የሠራችውን መሠዊያ አይመለከትም፥ ጣቶቹም ወደ አበጁአቸው፥ ወደ ማምለኪያ ዐፀዶች ወይም ወደ ፀሐይ ምስሎች፥ አያይም። 9በዚያም ቀን በእስራኤል ልጆች ፊት የአሞራውያንና የኤዊያውያን ከተሞች እንደ ተፈቱ፥ እንዲሁ ከተሞችህ ይፈታሉ፥ ባድማም ይሆናሉ። 10የደኅንነትህን አምላክ ረስተሃል፥ የረድኤትህንም ጌታ አላሰብህም፥ ስለዚህ ያማረውን ተክል ተክለሃል፥ እንግዳንም ዘር ዘርተሃል። 11በተከልህበት ቀን ታበቅለዋለህ፥ በነጋውም ዘርህን እንዲያብብ ታደርገዋለህ፥ ነገር ግን በኀዘንና በትካዜ ቀን መከሩ ይሸሻል። 12እንደ ባሕር ሞገድ ድምፅ ለሚተምሙ ለወገኖች ብዛት፥ እንደ ኃይለኛም ውኃ ጩኸት ለሚጮኹ አሕዛብ ወዮላቸው! 13አሕዛብ እንደ ብዙ ውኃ ጩኸት ይጮኻሉ፥ እርሱ ግን ይገሥጻቸዋል፥ እነርሱም እየሸሹ ይርቃሉ፥ በተራራም ላይ እንዳለ እብቅ በነፋስ ፊት፥ ዐውሎ ነፋስ እንደሚያዞረውም ትቢያ ይበተናሉ። 14በመሸ ጊዜ፥ እነሆ፥ ድንጋጤ አለ፥ ከማለዳም በፊት አይገኙም። የዘረፉን ሰዎች እድል ፈንታ፥ የበዘበዙንም ዕጣ ይህ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 17: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ