ትንቢተ ኢሳይያስ 14
14
1እግዚአብሔርም ያዕቆብን ይምረዋል፥ እስራኤልንም ደግሞ ይመርጠዋል፥ በአገራቸውም ያኖራቸዋል፥ መጻተኛም ከእርሱ ጋር ይተባበራል፥ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃል። 2አሕዛብም ይዘው ወደ ስፍራቸው ያመጡአቸዋል፥ የእስራኤልም ቤት በእግዚአብሔር ምድር እንደ ሎሌዎችና እንደ ገረዶች አድርገው ይገዙአቸዋል፥ የማረኩአቸውን ይማርካሉ፥ አስጨናቂዎችንም ይገዛሉ። 3በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፥ እግዚአብሔር ከኀዘንህና ከመከራህ ከተገዛህለትም ከጽኑ ባርነት ያሳርፍሃል። 4ይህንም ምሳሌ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ታነሣለህ እንዲህም ትላለህ፦ አስጨናቂ እንዴት አረፈ! አስገባሪም እንዴት ጸጥ አለ! 5-6አሕዛብንም በመዓትና በማያቋርጥ መምታት የመታውን፥ አሕዛብንም ባልተከለከለ መከራ በቍጣው የገዛውን የኀጥኣንን በትር የአለቆችንም ዘንግ እግዚአብሔር ሰብሮአል። 7ምድርም ሁሉ አርፋ በጸጥታ ተቀምጣለች እልልም ብላለች። 8ጥድና የሊባኖስ ዝግባ፦ አንተ ከተዋረድህ ጀምሮ ማንም ይቈርጠን ዘንድ አልወጣብንም ብለው በአንተ ደስ አላቸው። 9ሲኦል በመምጣትህ ልትገናኝህ በታች ታወከች፥ የሞቱትንም፥ የምድርንም ታላላቆች ሁሉ፥ ለአንተ አንቀሳቀሰች፥ የአሕዛብንም ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው አስነሣች። 10እነዚህ ሁሉ፦ አንተ ደግሞ እንደ እኛ ደክመሃልን? እኛንስ መስለሃልን? 11ጌጥህና የበገናህ ድምፅ ወደ ሲኦል ወረደ፥ በበታችህም ብል ተነጥፎአል፥ ትልም መደረቢያህ ሆኖአል ብለው ይመልሱልሃል። 12አንተ የንጋት ልጅ አጥቢያ ኮከብ ሆይ፥ እንዴት ከሰማይ ወደቅህ! አሕዛብንም ያዋረድህ አንተ ሆይ፥ እንዴትስ ከምድር ድረስ ተቆረጥህ! 13አንተም በልብህ፦ ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፥ 14ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ። 15ነገር ግን ወደ ሲኦል ወደ ጕድጓዱም ጥልቅ ትወርዳለህ። 16የሚያዩህ ይመለከቱሃልና፦ በውኑ ምድርን ያንቀጠቀጠ፥ መንግሥታትንም ያናወጠ፥ 17ዓለሙን ባድማ ያደረገ፥ ከተሞችንም ያፈረሰ፥ ምርኮኞቹንም ወደ ቤታቸው ያልሰደደ ሰው ይህ ነውን? ብለው ያስተውሉሃል። 18የአሕዛብ ነገሥታት ሁሉ በየቤታቸው በክብር አንቀላፍተዋል። 19አንተ ግን እንደ ተጠላ ቅርንጫፍ ከመቃብርህ ተጥለሃል፥ በሰይፍም የተወጉት፥ ተገድለውም ወደ ጕድጓዱ ድንጋዮች የወረዱ ከድነውሃል፥ እንደተረገጠም ሬሳ ሆነሃል። 20ምድርህን አጥፍተሃልና፥ ሕዝብህንም ገድለሃልና ከእነርሱ ጋር በመቃብር በአንድነት አትሆንም፤ የክፉዎች ዘር ለዘላለም የተጠራ አይሆንም። 21እንዳይነሱም፥ ምድርንም እንዳይወርሱ፥ የዓለሙንም ፊት በከተሞች እንዳይሞሉ ስለ አባቶቻቸው በደል ለልጆቹ ሞትን አዘጋጁላቸው። 22በእነርሱ ላይ እነሣለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ከባቢሎን ስምንና ቅሬታን፥ ዘርንና ትውልድንም እቈርጣለሁ ይላል እግዚአብሔር። 23የጃርት መኖርያ የውሃም መቋሚያ አደርጋታለሁ፥ በጥፋትም መጥረጊያ እጠርጋታለሁ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 24የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል፦ እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፥ እንዳሰብሁም እንዲሁ ይቆማል። 25አሦርን በምድሬ ላይ እሰብራለሁ፥ በተራራዬም ላይ እረግጠዋለሁ፥ ቀንበሩም ከእነርሱ ላይ ይነሳል፥ ሸክሙም ከጫንቃቸው ላይ ይወገዳል። 26በምድር ሁሉ ላይ እግዚአብሔር ያሰበው አሳብ ይህ ነው፥ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋች እጅ ይህች ናት። 27የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይህን አስቦአል፥ የሚያስጥለውስ ማን ነው? አጁም ተዘርግታለች፥ የሚመልሳትስ ማን ነው? 28ንጉሡ አካዝ በሞተበት ዘመን ይህ ሸክም ሆነ። 29ፍልስጥኤም ሆይ፥ ከእባቡ ሥር እፉኝት ይወጣልና፥ ፍሬውም የሚበርርና እሳት የሚመስል እባብ ይሆናልና የመታሽ በትር ስለ ተሰበረ ሁላችሁም ደስ አይበላችሁ። 30የድሆችም የበኵር ልጆች ይሰማራሉ፥ ችግረኞችም ተዘልለው ይተኛሉ፥ ሥርህንም በራብ እገድላለሁ፥ ቅሬታህም ይገደላል። 31አንተ በር ሆይ፥ ወዮ በል፥ አንቺም ከተማ ሆይ፥ ጩኺ፥ ፍልስጥኤም ሆይ፥ ሁላችሁም ቀልጣችኋል፥ ጢስ ከሰሜን ይመጣል ከጭፍራውም ተለይቶ የሚቀር የለም። 32ለሕዝቡም መልእክተኞች ምን ብሎ መመለስ ይገባል? እግዚአብሔር ጽዮንን እንደ መሠረተ፥ የሕዝቡም ችግረኞች በእርስዋ ውስጥ እንደሚጠጉ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ