ትንቢተ ሆሴዕ 14
14
1እስራኤል ሆይ፥ በኃጢአትህ ወድቀሃልና ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ። 2ከእናንተ ጋር ቃልን ውሰዱ፥ ወደ እግዚአብሔርም ተመልሳችሁ፦ ኃጢአትን ሁሉ አስወግዱ፥ በቸርነትም ተቀበለን፥ በወይፈንም ፋንታ የከንፈራችንን ፍሬ እንሰጣለን። 3አሦር አያድነንም፥ በፈረስ ላይ አንቀመጥም፥ ድሀ አደጉም በአንተ ዘንድ ምሕረትን ያገኛልና ከእንግዲህ ወዲህ ለእጆቻችን ሥራ፦ አምላኮቻችን ናችሁ አንላቸውም በሉት።
4ቍጣዬ ከእርሱ ዘንድ ተመልሶአልና ዓመፃቸውን እፈውሳለሁ፥ በገዛ ፈቃዴ እወድዳቸዋለሁ። 5ለእስራኤልም እንደ ጠል እሆነዋለሁ፥ እንደ አበባም ያብባል፥ እንደ ሊባኖስም ሥሩን ይሰድዳል። 6ቅርንጫፎቹም ይዘረጋሉ፥ ውበቱም እንደ ወይራ፥ ሽታውም እንደ ሊባኖስ ይሆናል። 7ከጥላውም በታች የሚቀመጡ ይመለሳሉ፥ ከእህሉም የተነሣ ይጠግባሉ፥ እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ፥ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል። 8ከእንግዲህ ወዲያ ጣዖት ለኤፍሬም ምንድር ነው? እኔ ሰምቼዋለሁ፥ ወደ እርሱም እመለከታለሁ፥ እኔ እንደ ለመለመ ጥድ ነኝ፥ ፍሬህ በእኔ ዘንድ ይገኛል።
9ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፥ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፥ ጻድቃንም ይሄዱበታል፥ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 14: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ