ትንቢተ ሆሴዕ 1
1
1በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስም ዘመን በእስራኤልም ንጉሥ በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም ዘመን ወደ ብኤሪ ልጅ ወደ ሆሴዕ የመጣ የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።
2እግዚአብሔር መጀመሪያ በሆሴዕ በተናገረ ጊዜ፥ እግዚአብሔር ሆሴዕን፦ ምድሪቱ ከእግዚአብሔር ርቃ ታላቅ ግልሙትና ታደርጋለችና ሂድ፥ ጋለሞታን ሴትና የግልሙትናን ልጆች ለአንተ ውሰድ አለው። 3እርሱም ሄዶ የዴቤላይምን ልጅ ጎሜርን አገባ፥ እርስዋም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደችለት። 4እግዚአብሔርም፦ ከጥቂት ዘመን በኋላ የኢይዝራኤልን ደም በኢዩ ቤት ላይ እበቀላለሁና፥ ከእስራኤልም ቤት መንግሥትን እሽራለሁና ስሙን ኢይዝራኤል ብለህ ጥራው፥ 5በዚያም ቀን በኢይዝራኤል ሸለቆ ውስጥ የእስራኤልን ቀስት እሰብራለሁ አለው። 6ደግሞ ፀነሰች ሴት ልጅንም ወለደች። እግዚአብሔርም፦ ይቅር እላቸው ዘንድ የእስራኤልን ቤት ከእንግዲህ ወዲህ አልምርምና ስምዋን ሎሩሃማ ብለህ ጥራት፥ 7ነገር ግን የይሁዳን ቤት እምራለሁ፥ በአምላካቸው በእግዚአብሔር አድናቸዋለሁ እንጂ በቀስት ወይም በሰይፍ ወይም በሰልፍ ወይም በፈረሶች ወይም በፈረሰኞች አላድናቸውም አለው። 8ሎሩሃማም ጡት ባስጣለች ጊዜ፥ ደግሞ ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች። 9እግዚአብሔርም፦ ሕዝቤ አይደላችሁምና፥ እኔም አምላክ አልሆናችሁምና ስሙን ሎዓሚ ብለህ ጥራው አለው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 1: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ