ትንቢተ ዕንባቆም 2
2
1በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፥ የሚናገረኝንም፥ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ። 2እግዚአብሔርም መለሰልኝ እንዲህም አለ፦ አንባቢው ይፈጥን ዘንድ ራእዩን ጻፍ፥ በጽላትም ላይ ግለጠው። 3ራእዩ ገና እስከ ተወሰነው ጊዜ ነው፥ ወደ ፍጻሜውም ይቸኵላል፥ እርሱም አይዋሽም፥ ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፥ እርሱ አይዘገይም።
4እነሆ፥ ነፍሱ ኰርታለች፥ በውስጡም ቅን አይደለችም፥ ጻድቅ ግን በእምነቱ በሕይወት ይኖራል። 5እርሱ አታላይና ኵሩ ሰው ነው፥ በስፍራው ዐርፎ አይቀመጥም፥ ስስቱን እንደ ሲኦል ያሰፋል፥ እርሱም እንደ ሞት አይጠግብም፥ አሕዛብንም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበስባል፥ ወገኖቹንም ሁሉ ወደ እርሱ ያከማቻል። 6እነዚህ ሁሉ፦ ለእርሱ ያልሆነውን ወደ እርሱ ለሚሰበስብ መያዣውንም ለራሱ የሚያበዛ ወዮለት! እስከ መቼ ነው? እያሉ ምሳሌ አይመስሉበትምን? 7ተረትም አይተርቱበትምን? የሚነክሱህ ድንገት አይነሡብህምን? የሚያስጨንቁህም ይነቃሉ፥ ለእነርሱም ብዝበዛ ትሆናለህ። 8የሰውን ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ አንተ ብዙዎችን አሕዛብን በዝብዘሃልና ከአሕዛብ የቀሩት ሁሉ ይበዘብዙሃል።
9ከክፉ እንዲድን ጐጆውን በከፍታ ላይ ያደርግ ዘንድ ለቤቱ ክፉ ትርፍን ለሚሰበስብ ወዮለት! 10ብዙ አሕዛብን አጥፍተሃልና ለቤትህ እፍረትን መክረሃል፥ በነፍስህም ላይ ኃጢአትን አድርገሃል። 11ድንጋይም ከግንብ ውስጥ ይጮኻል፥ እንጨትም ከውቅር ውስጥ ይመልስለታል።
12ከተማን በደም ለሚሠራ፥ ከተማንም በኃጢአት ለሚመሠርት ወዮለት! 13እነሆ፥ አሕዛብ ስለ እሳት እንዲሠሩ፥ ወገኖችም ስለ ከንቱነት እንዲደክሙ ከሠራዊት ጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ አይደለምን? 14ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና።
15ኅፍረተ ሥጋውን ለማየት ባልንጀራውን ለሚያጠጣ፥ ክፉንም ለሚጨምርበት፥ ለሚያሰክረውም ወዮለት! 16በክብር ፋንታ እፍረት ሞልቶብሃል፥ አንተ ደግሞ ጠጥተህ ተንገድገድ፥ የእግዚአብሔር የቀኙ ጽዋ ይመለስብሃል፥ እፍረትም በክብርህ ላይ ይሆናል። 17የሰውንም ደም ስላፈሰስህ፥ በምድሪቱና በከተማይቱም በእርስዋም በሚኖሩ ሁሉ ላይ ስላደረግኸው ግፍ፥ በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ይከድንሃል፥ የአራዊትም አደጋ ያስፈራራሃል።
18የተቀረጸውን ምስል ሠሪው የቀረጸው ለምን ጥቅም ነው? ዲዳንም ጣዖት ይሠራ ዘንድ ሠሪው የታመነበቱ፥ ሐሰትን የሚያስተምር ቀልጦ የተሠራ ምን ይጠቅማል? 19እንጨቱን፦ ንቃ፥ ዲዳውንም ድንጋይ፦ ተነሣ ለሚለው ወዮለት! በውኑ ይህ ያስተምራልን? እነሆ፥ በወርቅና በብር ተለብጦአል፥ ምንም እስትንፋስ የለበትም። 20እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፥ ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል።
Currently Selected:
ትንቢተ ዕንባቆም 2: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ