የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 38

38
1በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ ይሁዳ ከወንድሞቹ ተለይቶ ወረድ፥ ስሙን ኤራስ ወደሚሉት ወደ ዓዶሎማዊውም ሰው ገባ። 2ከዚያም ይሁዳ የከነዓናዊውን የሴዋን ሴት ልጅ አየ ወሰዳትም ወደ እርስዋም ገባ። 3ፀነሰችም ወንድ ልጅንም ወለደች ስሙንም ዔር ብላ ጠራችው። 4ደግሞም ፀነሰች ወንድ ልጅንም ወለደች ስሙንም አውናን ብላ ጠራችው። 5እንደ ገና ደግሞ ወንድ ልጅን ወለደች ስሙንም ሴሎም ብላ ጠራችው እርሱንም በወለደች ጊዜ ክዚብ በሚባል አገር ነበረች። 6ይሁዳም ለበኵር ልጁ ለዔርትዕማር የምትባል ሚስት አጋባው። 7የይሁዳም የበኵር ልጅ ዔር በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነበረ፤ እግዚአብሔር ቀሠፈው። 8ይሁዳም አውናን፦ ወደ ወንድምህ ሚስት ግባ አግባትም ለወንድምህም ዘርን አቁምለት አለው። 9አውናንም ዘሩ ለእርሱ እንዳይሆን አወቀ ወደ ወንድሙ ሚስት በገባ ጊዜ ለወንድሙ ዘር እንዳይስጥ ዘሩን በምድር ያፈስሰው ነበር። 10ይህም ሥራው በእግዚአብሔር ዘንድ ክፋ ሆነበት፥ እርሱንም ደግሞ ቀሠፈው። 11ይሁዳም ምራትን ትዕማርን፦ ልጄ ሴሎም እስኪያድግ ድረስ በአባትሽ ቤት መበለት ሆነሽ ተቀመጪ አላት እርሱ ደግሞ እንደ ወንድሞቹ እንዳይሞት ብሎአልና። ትዕማርም ሄዳ በአባትዋ ቤት ተቀመጠች።
12ከብዙ ዘመንም በኍላ የይሁዳ ሚስት የሴዋ ልጅ ሞተች ይሁዳም ተጽናና የበጎቹን ጠጕር ወደሚሸልቱት ሰዎችም ወደ ተምና ወጣ እርሱም ዓዶሎማዊው ወዳጁም ኤራስ። 13ለትዕማርም፦ እነሆ አማትሽ ይሁዳ የበጎቹን ጠጕር ይሸልት ዘንድ ወደ ተምና ይወጣል ብለው ነገሩአት። 14እርስዋም የመበለትነትዋን ልብስ አወለቀች፥ መጎናጸፊያዋንም ወሰደች ተሸፈነችም ወደ ተምናም በሚወስደው መንገድ ዳር በኤናይም ደጅ ተቀመጠች ሴሌም እንደ አደገ ሚስትም እንዳልሆነችው አይታለችና። 15ይሁዳም ባያት ጊዜ ጋለሞታን መሰለችው ፊትዋን ተሸፍና ነበርና። 16ወደ እርስዋም አዘነበለ፦ እባክሽ ወደ አንቺ ልግባ አላት እርስዋ ምራቱ እንደ ሆነች አላወቀም ነበርና። እርስዋም፦ ወደ እኔ ብትገባ ምን ትሰጠኛለህ? አለችው። 17የፍየል ጠቦት ከመንጋዬ እሰድድልሻለሁ አላት። እርስዋም፦ እስክትሰደድልኝ ድረስ መያዣ ትሰጠኛለህን? አለችው። 18እርሱም፦ ምን መያዣ ልስጥሽ? አላት። እርስዋም፦ ቀለበትህን አምባርህን በእጅህ ያለውን በትር አለች እርሱም ሰጣትና ከእርስዋ ደረሰ እርስዋም ፀነሰችለት። 19ኤስውም ተነሥታ ሄደች መጎናጸፊያዋንም አውልቃ የመበለትነትዋን ልብስ ለበስች። 20ይሁዳም መያዣውን ከሴቲቱ እጅ ይቀበል ዘንድ በወዳጁ በዓዶሎማዊው እጅ የፍየሉን ጠቦት ላከላት እርስዋንም፥ አላገኛትም። 21እርሱም የአገሩን ሰዎች፦ በኤናይም በመንገድ ዳር ተቀምጣ የነበረች ጋለሞታ ወዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው። 22እነርሱም፦ በዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉት። ወደ ይሁዳም ተመልሶ እንዲህ አለው፦ አላገኘኍትም የአገሩም ሰዎች ደግሞ፦ ከዚህ ጋለሞታ አልነበረችም አሉኝ። 23ይሁዳም፦ እኛ መዘበቻ እንዳንሆን ትውሰደው እነሆ የፍየሉን ጠቦት ሰደድሁላት አንተም አላገኘሃትም አለ።
24እንዲህም ሆን ከሦስት ወር በኍላ ለይሁዳ፦ ምራትህ ትዕማር ሴሰነች፤ ደግሞም በዝሙት እነሆ ፀነሰች ብለው ነገሩት። ይሁዳም፦ አውጡአትና በእሳት ትቃጠል አለ። 25እርስዋም ባወጡአት ጊዜ ወደ አማትዋ እንዲህ ብላ ላከች፦ ለዚህ ለባለ ገንዘብ ነው የፀነስሁት፤ ተመልከት፤ ይህ ቀለበት ይህ አምባር፤ ይህ በትር የማን ነው? 26ይሁዳም አወቀ፦ ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነትኛ ሆነች ልጄን ሴሎምን አልሰጠኍትምና አለ። ደግሞም አላወቃትም። 27በመውለጃዋም ጊዜ እነሆ መንታ ልጆች በሆድዋ ነበሩ። 28ስትውልድም አንድ እጁን አወጣ አዋላጂቱም ቀይ ፈትል ወስዳ በእጁ አስረች፦ ይህ መጀመሪያ ይወጣል አለች። 29እንዲህም ሆነ እጁን በመለሰ ጊዜ እነሆ ወንድሙ ወጣ፤ እርስዋም፦ ለምን ጥስህ ወጣህ? አለች፤ 30ስሙንም ፋሬስ ብላ ጠራችው። ከእርሱም በኍላ ቀይ ፈትል በእጁ ያለበት ወንድሙ ወጣ ስሙም ዛራ ተባለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ