የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 30

30
1ራሔልም ለያዕቆብ ልጆችን እንዳልወለደች ባየች ጊዜ በእኅትዋ ቀናችባት፤ ያቆብንም፦ ልጅ ስጠኝ፤ ይህስ ካልሆነ እሞታለሁ አለችው። 2ያዕቆብም ራሔልን ተቆጥቶ፦ በውኑ እኔ የሆድን ፍሬ በነሣሽ በእግዚአብሔር ቦታ ነኝን? አላት። 3እርስዋምም ባሪያዬ ባላ እነሆ አለች፤ ድረስባት፤ በእኔም ጭን ላይ ትውለድ፥ የእርስዋም ልጆች ለእኔ ደግሞ ይሁኑልኝ አለች። 4ባሪያዋን ባላንም ሚስት ትሆነው ዘንድ ለእርሱ ሰጠችው፤ ያዕቆብም ደረሰባት። 5ባላም ፀነሰች፥ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደችለት። 6ራሔልም፦ እግዚአብሔር ፈረደልኝ፥ ቃሌንም ደግሞ ሰማ፥ ወንድ ልጅንም ስጠኝ አለች፤ ስለዚህ ስሙን ዳን ብላ ጠራችው። 7የራሔልም ባሪያ ባላ ደግማ ፀነሰች፥ ለያዕቆብም ሁለተኛ ወንድ ልጅን ወለደች። 8ራሔልም፦ ብርቱ ትግልን ከእኅቴ ጋር ታገልሁ፥ አሸነፍሁም አለች፤ ስሙንም ንፍታሌም ብላ ጠራችው።
9ልያም መውለድን እንዳቆመች ባየች ጊዜ ባሪያዋን ዘለፋን ወሰደች፥ ሚስት ትሆንውም ዘንድ ለያዕቆብ ሰጠችው። 10የልያ ባሪያ ዘለፋም ወንድ ልጅን ለያዕቆብ ወለደች። 11ልያም፦ ጉድ አለች ስሙንም ጋድ ብላ ጠራችው። 12የልያ ባሪያ ዘለፋም ዳግመኛ ለያዕቆብ ወንድ ልጅን ወለደች። 13ልያም፦ ደስታ ሆነልኝ፤ ሴቶች ያመሰግኑኛልና አለች፤ ስሙንም አሴር ብላ ጠራችው። 14ሮቤልም ስንዴ በሚታጨድበት ወራት ወጣ፥ በእርሻም እንኮይ አገኘ፥ ለእናቱ ለልያም አመጣላት። 15ራሔልም ልያን፦ የልጅሽን እንኮይ ስጪኝ አለቻት። እርስዋም፦ ባሌን መውሰድሽ በውኑ ጥቂት ነገር ነውን? አሁን ደግሞ የልጄን እንኮይ ልትወስጂ ትፈልጊአለሽን? አለቻት። ራሔልም፦ እንኪያስ ስለ ልጅሽ እንኮይ በዚህች ሌሊት ከአንቺ ጋር ይተኛ አለች። 16ያዕቆብ ሲመሽ ከዱር ገባ፥ ልያም ልትቀበለው ወጣች እንዲህም አለችው፦ ወደ እኔ ትገባለህ፤ በልጄ እንኮይ በእርግጥ ተከራይቼሃለሁና። በዚያችም ሌሊት ከእርስዋ ጋር ተኛ። 17እግዚአብሔርም የልያን ጸሎት ሰማ፥ ፀነሰችም፥ አምስትኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች። 18ልያም ባሪያዬን ለባሌ ስለ ሰጠሁ እግዚአብሔር ዋጋዬን ሰጠኝ አለች፤ ስሙንም ይሳኮር ብላ ጠራችው። 19ልያም ደግማ ፀነሰች፥ ስድስተኛ ወንድ ልጅንም ለያዕቆብ ወለደች 20ልያም፦ እግዚአብሔር መልካም ስጦታን ሰጠኝ፤ እንግዲህስ ባሌ ከእኔ ጋር ይኖራል፥ ስድስት ልጆችን ወልጄለታለሁና አለች፤ ስሙንም ዛብሎን ብላ ጠራችው። 21ከዚያም በኋላ ሴት ልጅን ወለደች፤ ስምዋንም ዲና አለቻት። 22እግዚአብሔር ራሔልን አሰበ፥ እግዚአብሔርም ተለመናት፥ ማኅፀንዋንም ከፈተላት፤ 23ፀነሰችም፥ ወንድ ልጅንም ወለደችና፦ እግዚአብሔር ስድቤን አስወገደ አለች፤ 24ስሙንም፦ እግዚአብሔር ሁለተኛ ወንድ ልጅን ይጨምርልኝ ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው።
25ራሔልም ዮሴፍን ከወለደች በኋላ ያዕቆብ ላባን እንዲህ አለው፦ ወደ ስፍራዬ ወደ አገሬም እመለስ ዘንድ አሰናብተኝ። 26ስለ እነርሱ የተገዛሁላቸውን ሚስቶችንና ልጆቼን ስጠኝና ልሂድ፤ የተገዛሁልህን መገዛት ታውቃለህና። 27ላባም፦ በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚህ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና አለው። 28ደመወዝህን ንገረኝ፥ እርሱንም እሰጥሃለሁ አለ። 29እርሱም አለው፦ እንዴት እንዳገለገልሁህ፥ ከብትህንም እንዴት እንደ ጠበቅሁልህ አንተ ታውቃለህ። 30ከእኔ መምጣት በፊት የነበረህ ጥቂት ነበርና፥ ዛሬም እጅግ በዛ፤ ወደ አንተ በመምጣቴ እግዚአብሔር ባረክህ፤ አሁንም እኔ ደግሞ ለቤቴ የምሠራው መቼ ነው? 31እርሱም፦ የምሰጥህ ምንድር ነው? አለ። ያዕቆብም አለው፦ ምንም አትስጠኝ፤ ይህንም ነገር ብታደርግልኝ እንደ ገና በጎችህን አበላለሁ እጠብቃለሁም። 32ዛሬ በመንጎችህ በኩል አልፋለሁ፥ በዚያም ከበጎችህ መካከል ዝንጉርጉርና ነቍጣ ያለበቱን ጥቁሩንም በግ ሁሉ፥ ከፍየሎቹም ነቍጣና ዝንጕርጕር እለያለሁ፤ እነርሱም ደመወዜ ይሆናሉ። 33ስለዚህም በፊትህ ያለውን ደመወዜን ለመመልከት በመጣህ ጊዜ ወደ ፊት ጻድቅነቴ ይመሰክርልኛል፤ ከፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ የሌለበት ከበግ ጠቦቶችም ጥቁር ያልሆኑ ሁሉ፥ እርሱ በእኔ ዘንድ ቢገኝ እንደ ተሰረቀ ይቆጠርብኝ። 34ላባም፦ እነሆ እንደ ቃልህ ይሁን አለ። 35በዚያም ቀን ከተባቶቹ ፍየሎች ሽመልመሌ መሳይና ነቍጣ ያለባቸውን፥ ከእንስቶቹም ፍየሎች ዝንጕርጕርና ነቍጣ ያለባቸውን ነጭ ያለበትን ማንኛውንም ሁሉ ከበጎቹም መካከል ጥኩሩን በግ ሁሉ ለይቶ ለልጆቹ ሰጣቸው። 36በእርሱና በያዕቆብ መካከልም የሦስት ቀን መንገድ ያህል አራቃቸው፤ ያዕቆብም የቀሩትን የላባን በጎች ይጠብቅ ነበር።
37ያዕቆብም ልብን ለውዝ ኤርሞን ከሚባሉ እንጨቶች እርጥብ በትርን ወስዶ በበትሮቹ ውስጥ ያለውን ነጭ እንዲታይ ነጭ ሽመልመሌ አድርጎ ላጣቸው። 38የላጣቸውንም በትሮች በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ በበጎች ፊት አኖራቸው፤ በጎቹ ውኃ ሊጠጡ በመጡ ጊዜ ይጎመጁ ነበር። 39በጎቹም በትሮቹን አይተው ከመጎምጀውታቸው የተነሣ ፀነሱ፤ በጎቹም ሽመልመሌ መሳይና ዝንጕርጕር ነቍጣም ያለበቱን ወለዱ። 40ያዕቆብም ጠቦቶቹን ለየ፥ ሽመልመሌ መሳይና ጥቁር ያለባቸውን በጎቹንም ለብቻቸው አቆማቸው፥ ወደ ላባም በጎች አልጨመራቸውም። 41እንዲህም ሆነ፤ የበረቱት በጎች በጎመጁ ጊዜ፥ በጎቹ በትሮቹን አይተው በበትሮቹ አምሳል ይፀንሱ ዘንድ ያዕቆብ በትሮቹን በውኃ ማጠጫው ገንዳ ውስጥ ከበጎቹ ፊት አደረገ፤ 42በደከሙ በጎችም ፊት በትሩን አያደርገውም ነበር፤ የደከሙትም ለላባ የበረቱትም ለያዕቆብ ሆኑ 43ያ ሰውም እጅግ ባለ ጠጋ ሁነ፤ ብዙም ከብት ሴቶችም ወንዶችም ባሪያዎች ግመሎችም አህዮችም ሆኑለት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ