መጽሐፈ ዕዝራ 5
5
የቤተ መቅደሱ ግንባታ እንደገና እንደቀጠለ
1ነቢያቱም ሐጌና የአዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ለነበሩ አይሁድ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። 2በዚያን ጊዜም የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል እና የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ተነሥተው በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመሩ፤ የሚያግዙአቸውም የእግዚአብሔር ነቢያት ከእነርሱ ጋር ነበሩ። 3በዚያም ዘመን በወንዝ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ፥ ተባባሪዎቻቸውም ወደ እነርሱ መጥተው “ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንኑም ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው?” አሉአቸው። 4ደግሞም፦ “ይህንስ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ስም ማን ነው?” ብለው ጠየቁአቸው። 5የአምላካቸው ዓይን ግን በአይሁድ ሽማግሌዎች ላይ ነበረ፤ ይህም ነገር ወደ ዳርዮስ እስኪደርስ ድረስ፥ መልሱም በደብዳቤ እስኪመጣ ድረስ አልከለከሉአቸውም።
6በወንዙ ማዶ የነበረው ገዥ ተንትናይ፥ ደግሞ ሰተርቡዝናይ፥ ተባባሪዎቹና በወንዙ ማዶ የነበሩት አፈርስካውያን ወደ ንጉሡ ወዳ ዳርዮስ የላኩት የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነበረ። 7እንዲህም የሚል ደብዳቤ ላኩለት፦ “ለንጉሡ ለዳርዮስ ሙሉ ሰላም ይሁን፤ 8ወደ ይሁዳ አገር ወደ ታላቁም አምላክ ቤት እንደ ሄድን ንጉሡ ይወቅ፤ እርሱም በትልቅ ድንጋይ ተሠራ፤ በቅጥሩም ውስጥ እንጨት ተደረገ፤ ያም ሥራ በትጋት ይሠራል፤ በእጃቸውም ይከናወናል። 9እነዚያንም ሽማግሌዎች፦ ‘ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንስ ቅጥር ታድሱ ዘንድ ያዘዛችሁ ማን ነው?’ ብለን ጠየቅናቸው። 10ደግሞም እናስታውቅህ ዘንድ፥ በእነርሱም ያሉትን ሹሞች ስም እንጽፍልህ ዘንድ ስማቸውን ጠየቅን። 11እንደዚህም ብለው መለሱልን፦ ‘እኛ የሰማይና የምድር አምላክ ባሪያዎች ነን፤ ከብዙም ዘመን ጀምሮ ተሠርቶ የነበረውን፥ ታላቁም የእሥራኤል ንጉሥ ሠርቶ የፈጸመውን ቤት እንሠራለን። 12አባቶቻችንም የሰማይን አምላክ ካስቈጡ በኋላ በከለዳዊው በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እርሱም ይህን ቤት አፈረሰ፤ ሕዝቡንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ። 13ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዘ። 14ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ከነበረው መቅደስ የወሰደውን፥ ወደ ባቢሎንም መቅደስ ያፈለሰውን የእግዚአብሔርን ቤት የወርቅንና የብርን ዕቃ ንጉሡ ቂሮስ ከባቢሎን መቅደስ አውጥቶ ሰሳብሳር ለተባለው ለሹሙ ሰጠውና፦ 15“ይህን ዕቃ ይዘህ ሂድ፤ በኢየሩሳሌምም ባለው መቅደስ አኑረው፤ የእግዚአብሔርም ቤት በስፍራው ይሠራ” አለው። 16በዚያ ጊዜም ይህ ሰሳብሳር መጣ፤ በኢየሩሳሌምም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየተሠራ አልተጨረሰም።’ 17አሁንም ይህ ነገር በንጉሡ ዓይን መልካም ቢሆን ይህ የእግዚአብሔር ቤት በኢየሩሳሌም ይሠራ ዘንድ ከንጉሡ ከቂሮስ ታዝዞ እንደ ሆነ በባቢሎን ባለው በንጉሡ ቤተ መዛግብት ይመርመር፤ ስለዚህም ነገር ንጉሡ ፈቃዱን ይላክልን።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 5: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ