የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 22

22
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርዳለህን? ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰትዋን ሁሉ አስታውቃት። 3እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ እንዲትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ! 4ባፈሰስሽው ደም በድለሻል ባደረግሽውም ጣዖታት ረክሰሻል፥ ቀንሽን አቀረብሽ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፥ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ ለአገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። 5አንቺ ስምሽ የረከሰ ሽብርም የሞላብሽ ሆይ፥ ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል።
6እነሆ፥ የእስራኤል አለቆች እያንዳንዱ እንደ ችሎቱ ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ነበሩ። 7በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፥ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፥ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ። 8ቅድሳቴንም ናቅሽ ሰንበታቴንም አረከስሽ። 9ደምን ያፈስሱ ዘንድ ቀማኞች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፥ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፥ በመካከልሽ ሴሰኝነትን አደረጉ። 10በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፥ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ። 11ሰውም በባልንጀራው ሚስት ርኵሰትን አደረገ፥ አባትም የልጁን ሚስት አረከሰ፥ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አሳፈረ። 12በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ጉቦን ተቀበሉ፥ አንቺም አራጣና ትርፍ ወስደሻል፥ ከባልንጀሮችሽም በቅሚያ የስስትን ትርፍ አገኘሽ፥ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13ስለዚህ፥ እነሆ፥ አንቺ ባደረግሽው ስስት በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ እጄን አጨበጨብሁ። 14በውኑ እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጅሽ ትጸናለችን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ አደርገውማለሁ። 15ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ ወደ አገሮችም እዘራሻለሁ፥ ርኵሰትሽንም ከአንቺ ዘንድ አጠፋለሁ። 16በአሕዛብም ፊት አንቺ ትረክሻለሽ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂአለሽ።
17የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤል ቤት ለእኔ እንደ አተላ ሆኑብኝ፥ እነርሱ ሁሉ በከውር ውስጥ መዳብና ቈርቈሮ ብረትና እርሳስ ናቸው፥ የብር አተላ ናቸው። 19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ፥ እነሆ፥ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰብስባችኋለሁ። 20እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን ብረትንና እርሳስን ቈርቈሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፥ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ አቀልጣችሁማለሁ። 21አሰበስባችሁማለሁ የመዓቴንም እሳት አናፋባችኋለሁ በውስጡም ትቀልጣላችሁ። 22ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጡዋ ትቀልጣላችሁ፥ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ።
23የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24የሰው ልጅ ሆይ፦ አንቺ ያልነጻሽ በቁጣም ቀን ያልዘነበብሽ ምድር ነሽ በላት። 25በውስጥዋ ያሉ ነቢያት እንደሚጮኽና እንደሚናጠቅ አንበሳ አንድ ሆነው ተማማሉ፥ ነፍሶችን በልተዋል፥ ብልጥግናና ሀብትን ወስደዋል፥ በውስጥዋም መበለቶችን አብዝተዋል። 26ካህናቶችዋም ሕጌን በድለዋል ቅድሳቴንም አርክሰዋል፥ ቅዱስ በሆነና ቅዱስ ባልሆነ መካከልም አልለዩም፥ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውን ልዩነት አላስታወቁም፥ ዓይናቸውንም ከሰንበታቴ ሰወሩ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ። 27በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው። 28እግዚአብሔርም ሳይናገር ነቢያቶችዋ፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እያሉ ከንቱን ራእይ በማየት የሐሰትንም ምዋርት ለእነርሱ በማምዋረት ያለ ገለባ በጭቃ ይመርጓቸዋል። 29የምድርን ሕዝብ ግፍ አደረጉ ቅሚያም ሠሩ፥ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፥ መጻተኛውንም በደሉ። 30ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው በመካከላቸው ፈለግሁ፥ ነገር ግን አላገኘሁም። 31ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፥ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፥ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ