ትንቢተ ሕዝቅኤል 13
13
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት በሚናገሩ በእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፥ ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን፦ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ በላቸው፥ 3ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ምንምን ሳያዩ የገዛ መንፈሳቸውን ለሚከተሉ ለሰነፎች ነቢያት ወዮላቸው! 4እስራኤል ሆይ፥ ነቢያትህ በምድረ በዳ እንደሚኖሩ ቀበሮች ናቸው። 5ወደ ተሰበረው ቅጥር አልወጣችሁም፥ በእግዚአብሔርም ቀን በሰልፍ ትቆሙ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ቅጥር አልሠራችሁም። 6እግዚአብሔር ሳይልካቸው፦ እግዚአብሔር ይላል የሚሉ ሰዎች ከንቱ ነገርንና ውሸተኛ ምዋርትን አይተዋል፥ ቃሉም ይጠና ዘንድ ተስፋ አስደርገዋል። 7እኔም ሳልናገር፦ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎአል ስትሉ፥ ከንቱ ራእይን ያያችሁ ውሸተኛንም ምዋርት የተናገራችሁ አይደላችሁምን?
8ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ከንቱ ነገርን ስለ ተናገራችሁ ውሸተኛ ራእይንም ስላያችሁ፥ ስለዚህ፥ እነሆ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 9እጄም ከንቱ ራእይን በሚያዩ፥ በውሸትም በሚያምዋርቱ ነቢያት ላይ ትሆናለች፥ እነርሱም በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፥ በእስራኤልም ቤት መጽሐፍ አይጻፉም፥ ወደ እስራኤልም ምድር አይገቡም፥ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 10ሰላም ሳይኖር፦ ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፥ አንዱም ሰው ቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ፥ 11ገለባ በሌለበት ጭቃ ይመርጉታልና ገለባ በሌለበት ጭቃ ለሚመርጉት ሰዎች፦ ይወድቃል በላቸው። የሚያሰጥም ዝናብ ይዘንባል፥ ታላቅም የበረዶ ድንጋይ ይወድቃል፥ ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል። 12እነሆ፥ ግንቡ በወደቀ ጊዜ፦ የመረጋችሁት ጭቃ ወዴት አለ? አይሉአችሁምን? 13ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በመዓቴ በዐውሎ ነፋስ እሰነጣጥቀዋለሁ፥ ያጠፋውም ዘንድ በቍጣዬ የሚያሰጥም ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ይወርዳል። 14ገለባም በሌለበት ጭቃ የመረጋችሁትን ቅጥር አፈርሳለሁ ወደ ምድርም እጥለዋለሁ፥ መሠረቱም ይታያል። እርሱም ይናዳል በመካከሉም ትጠፋላችሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 15መዓቴንም በግንቡ ላይ ገለባም በሌለበት ጭቃ በመረጉት ላይ እፈጽማለሁ፥ እኔም፦ ግንቡና መራጊዎቹ የሉም እላችኋለሁ። 16እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የሚናገሩ የሰላምን ራእይ የሚያዩላት የእስራኤል ነቢያት ናቸው፥ ሰላምም የለም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
17አንተም፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ከገዛ ልባቸው ትንቢት በሚናገሩ በሕዝብህ ሴቶች ልጆች ላይ ፊትህን አድርግ ትንቢትም ተናገርባቸው፥ እንዲህም በል፦ 18ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነፍስን ለማጥመድ ለእጅ ድጋፍ ሁሉ መከዳ ለሚሰፋ ለሰውም ሁሉ ራስ እንደ እየቁመቱ ሽፋን ለሚሠሩ ሴቶች ወዮላቸው! የሕዝቤንም ነፍስ ብታጠምዱ በውኑ ነፍሳችሁን ታድናላችሁን? 19ውሸታችሁን ለሚሰሙት ሕዝቤ እየዋሻችሁ ሞት የማይገባቸውን ነፍሳት ትገድሉ ዘንድ በሕይወትም መኖር የማይገባቸውን ነፍሳት በሕይወት ታኖሩ ዘንድ ስለ ጭብጥ ገብስና ስለ ቍራሽ እንጀራ በሕዝቤ ዘንድ አርክሳችሁኛል።
20ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ ነፍሳትን እንደ ወፍ በምታጠምዱባት በመከዳችሁ ላይ ነኝ፥ ከክንዳችሁም ወስጄ እቀድዳታለሁ፥ እንደ ወፍም የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት እለቅቃለሁ። 21ሽፋኖቻችሁን ደግሞ እቀድዳለሁ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፥ ከዚያም ወዲያ በእጃችሁ ለመታደን አይሆኑም፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ። 22እኔም ያላሳዘንሁትን የጻድቁን ልብ በውሸት አሳዝናችኋልና፥ በሕይወትም ይኖር ዘንድ ከክፉ መንገድ እንዳይመለስ የኃጢአተኛውን እጅ አበርትታችኋልና 23ስለዚህ ከንቱን ራእይ እንግዲህ አታዩም ምዋርትንም አታምዋርቱም፥ ሕዝቤንም ከእጃችሁ አድናለሁ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 13: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ