እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው፤ አለውም፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር። የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ። ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያን ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታችሁም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፤ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፤ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ’”። ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ “ግባ፤ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር”። ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት፥ “እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? ይልቁንም እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ” ብሎ ተናገረ። እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፤ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው።
ኦሪት ዘጸአት 6 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 6:2-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos