የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 10

10
8) የአንበጣ መንጋ
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ግባ፤ በመካከላቸው እነዚህን ተአምራት ለማድረግ የእርሱንና የባሪያዎቹን ልብ አደንድኛለሁ። 2ይህንንም ያደረግሁት ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ግብፃውያንን እንደቀጣሁና ምን ዓይነት ተአምራትን እንዳደረግሁ መንገር ትችሉ ዘንድ ነው፤ በዚህም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።” 3ሙሴም አሮንም ወደ ፈርዖን ገቡ፤ አሉትም፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በፊቴ ለመዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ያገለግሉኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 4ሕዝቤን ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን፥ እነሆ ነገ በአገርህ አንበጣዎችን አመጣለሁ፤ 5የምድሩንም ፊት ይሸፍኑታልና ምድሩን ለማየት አይቻልም፤ ከበረዶውም አምልጦ የተረፈላችሁን ትርፍ ይበሉታል፤ ያደገላችሁንም የእርሻውን ዛፍ ሁሉ ይበሉታል፤ 6ቤቶችህም የባሪያዎችህም ሁሉ ቤቶች የግብፃውያንም ሁሉ ቤቶች በእነርሱ ይሞላል፤ አባቶችህ የአባቶችህም አባቶች በምድር ላይ ከተቀመጡበት ቀን ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ እንደ እርሱ ያለ ያላዩት ነው።’” ተመልሶም ከፈርዖን ዘንድ ወጣ። 7የፈርዖንም ባሪያዎች፦ “ይህ ሰው እስከ መቼ ዕንቅፋት ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን ያገለግሉት ዘንድ ሰዎችን ልቀቅ ግብፅስ እንደ ጠፋች ገና አታውቅምን? አሉት።” 8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን መልሶ አስመጣቸው፤ ሂዱ፤ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን የሚሄዱት እነማን ናቸው?” አላቸው። 9ሙሴም፦ “እኛ እንሄዳለን፤ የእግዚአብሔርም በዓል ሆኖልናልና ታናናሾቻችንና ሽማግሌዎቻችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም፥ በጎቻችንና ከብቶቻችንም ከእኛ ጋር ይሄዳሉ፤” አለ። 10ፈርዖንም፦ “እናንተን ከልጆቻችሁ ጋር ስለቅቅ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ ነገር ግን ክፉ ነገር በአእምሮአችሁ እንዳለ እወቁ። 11እንዲህም አይይደለም፤ እናንተ ወንዶቹ ሂዱ፤ ይህን ፈልጋችኋልና እግዚአብሔርን አገልግሉ፤” አላቸው። ከፈርዖንም ፊት አባረሩአቸው።
12እግዚአብሔርም ሙሴን “በግብፅ አገር ላይ እንዲወጡ፥ ከበረዶውም የተረፈውን የምድርን ቡቃያ ሁሉ እንዲበሉ፥ ስለ አንበጣዎች በግብፅ አገር ላይ እጅህን ዘርጋ፤” አለው። 13ሙሴም በግብፅ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም የምሥራቅን ነፋስ ያን ቀን ሁሉና ሌሊቱን ሁሉ አመጣ፤ ማለዳም በሆነ ጊዜ የምሥራቁ ነፋስ አንበጣዎቹን አመጣ። 14አንበጣዎችም በግብፅ አገር ሁሉ ላይ ወጡ፤ በግብፅም ዳርቻ ሁሉ ላይ ተቀመጡ፤ እጅግም ብዙ ነበሩ፤ ይህንም የሚያህል አንበጣ በፊት አልነበረም፤ ወደፊትም ደግሞ እንደ እርሱ አይሆንም። 15የምድሩንም ፊት ፈጽመው ሸፈኑት፤ አገሪቱም ጨለመች፤ የአገሪቱን ቡቃያ ሁሉ በረዶውም የተወውን በዛፉ የነበረውን ፍሬ ሁሉ በሉ፤ ለምለም ነገር ዛፍም የምድር ሣርም በግብፅ አገር ሁሉ አልቀረም። 16ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን በፍጥነት ጠራ፤ “አምላካችሁን እግዚአብሔርን እናንተንም በደልሁ። 17አሁን እንግዲህ በዚህ ጊዜ ብቻ ኃጢአቴን ይቅር በሉኝ፤ ይህንም ሞት ብቻ ከእኔ ያነሣልኝ ዘንድ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑ አላቸው፤” 18ሙሴም ከፈርዖን ፊት ወጣ፤ ወደ እግዚአብሔርም ለመነ። 19እግዚአብሔርም ከምዕራብ ዐውሎ ነፋሱን አስወገደ፤ አንበጣዎቹንም ወስዶ በኤርትራ ባሕር ውስጥ ጣላቸው፤ አንድ አንበጣም በግብፅ ዳርቻ ሁሉ አልቀረም። 20እግዚአብሔርም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ የእስራኤልንም ልጆች አልለቀቀም።
9) ጨለማ
21እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ፤ በግብፅም አገር ላይ ሰው የሚዳስሰው ፅኑ ጨለማ ይሁን አለው። 22ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፥ በግብፅም አገር ሁሉ ላይ ፅኑ ጨለማ ሦስት ቀን ሆነ። 23ማንም ወንድሙን አላየም፤ ሦስት ቀንም ሙሉ ከስፍራው ማንም አልተነሣም፤ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ግን በተቀመጡበት ስፍራ ብርሃን ነበራቸው። 24ፈርዖንም ሙሴን ጠርቶ፦ “ሂዱ፤ እግዚአብሔርን አገልግሉ፤ ነገር ግን በጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ተዉ፤ ልጆቻችሁ ደግሞ ከእናንተ ጋር ይሂዱ፤” አለው። 25ሙሴም፦ “አንተ ደግሞ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምንሠዋው መሥዋዕትንና የሚቃጠል መሥዋዕትን ትሰጠናለህ። 26አምላካችንን እግዚአብሔርን ለማገልገል ከእነርሱ እንወስዳለንና ከብቶቻችን ከእኛ ጋር ይሄዳሉ፤ አንድ ሰኮናም አይቀርም፤ አምላካችን የምናገለግለው ምን እንደሆነ ከዚያ እስክንደርስ አናውቅም፤” አለ። 27እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አጸና፤ ሊለቅቃቸውም አልወደደም። 28ፈርዖንም፦ “ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ፊቴን ባየህበት ቀን ትሞታለህና ፊቴን እንዳታይ ተጠንቀቅ፤” አለው። 29ሙሴም፦ “እንደ ተናገረህ ይሁን፤ ፊትህን እንደ ገና አላይም፤” አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ