መጽሐፈ አስቴር 7
7
1ንጉሡና ሐማም ከንግሥቲቱ ከአስቴር ጋር ለመጠጣት መጡ። 2በሁለተኛውም ቀን ንጉሡ በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን፦ ንግሥት አስቴር ሆይ፥ የምትለምኚኝ ምንድር ነው? ይሰጥሻል፥ የምትሺውስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል አላት። 3ንግሥቲቱም አስቴር መልሳ፦ ንጉሥ ሆይ፥ በአንተ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ንጉሡንም ደስ ቢያሰኘው፥ ሕይወቴ በልመናዬ ሕዝቤም በመሻቴ ይሰጠኝ፥ 4እኔና ሕዝቤ ለመጥፋትና ለመገደል ለመደምሰስም ተሸጠናልና። ባርያዎች ልንሆን ተሸጠን እንደ ሆነ ዝም ባልሁ ነበር፥ የሆነ ሆኖ ጠላቱ የንጉሡን ጉዳት ለማቅናት ባልቻለም ነበር አለች። 5ንጉሡም አርጤክስስ ንግሥቲቱን አስቴርን፦ ይህን ያደርግ ዘንድ በልቡ የደፈረ ማን ነው? እርሱስ ወዴት ነው? ብሎ ተናገራት። 6አስቴርም፦ ያ ጠላትና ባለጋራ ሰው ክፉው ሐማ ነው አለች። ሐማም በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት ደነገጠ። 7ንጉሡም ተቈጥቶ የወይን ጠጅ ከመጠጣቱ ተነሣ፥ ወደ ንጉሡም ቤት አታክልት ውስጥ ሄደ። ሐማም ከንጉሡ ዘንድ ክፉ ነገር እንደ ታሰበበት አይቶአልና ከንግሥቲቱ ከአስቴር ሕይወቱን ይለምን ዘንድ ቆመ። 8ንጉሡም ከቤቱ አታክልት ወደ ወይን ጠጁ ግብዣ ስፍራ ተመለሰ፥ ሐማም አስቴር ባለችበት አልጋ ላይ ወድቆ ነበር። ንጉሡም፦ ደግሞ በቤቴ በእኔ ፊት ንግሥቲቱን ይጋፋታልን? አለ። ይህም ቃል ከንጉሡ አፍ በወጣ ጊዜ የሐማን ፊት ሸፈኑት። 9በንጉሡም ፊት ካሉት ጃንደረቦች አንዱ ሐርቦና፦ እነሆ ሐማ ለንጉሡ በጎ ለተናገረው ለመርዶክዮስ ያሠራው ርዝመቱ አምሳ ክንድ የሆነው ግንድ በሐማ ቤት ተተክሎአል አለ። ንጉሡም፦ በእርሱ ላይ ስቀሉት አለ። 10ሐማንም ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው ግንድ ላይ ሰቀሉት፥ በዚያም ጊዜ የንጉሡ ቍጣ በረደ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ