መጽሐፈ አስቴር 5
5
1በሦስተኛውም ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ በንጉሡ ቤት ትይዩ በንጉሡ ቤት በውስጠኛው ወለል ቆመች፥ ንጉሡም በቤቱ መግቢያ ትይዩ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በንጉሡ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር። 2ንጉሡም ንግሥቲቱ አስቴር በወለሉ ላይ ቆማ ባየ ጊዜ በዓይኑ ሞገስ አገኘች፥ ንጉሡም በእጁ የነበረውን የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፥ አስቴርም ቀርባ የዘንጉን ጫፍ ነካች።
3ንጉሡም፦ ንግሥት አስቴር ሆይ፥ የምትለምኚኝ ምንድር ነው? የምትሺውስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል አላት። 4አስቴርም፦ ለንጉሡ መልካም ሆኖ ቢታይ ንጉሡ ወዳዘጋጀሁለት ግብዣ ከሐማ ጋር ዛሬ ይምጣ አለች። 5ንጉሡም፦ አስቴር እንዳለች ይደረግ ዘንድ ሐማን አስቸኵሉት አለ። ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ። 6ንጉሡም በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን፦ የምትሺው ምንድር ነው? ይሰጥሻል፥ ልመናሽስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል አላት። 7አስቴርም መልሳ፦ ልመናዬና የምሻው ነገር ይህ ነው፥ 8በንጉሡ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ልመናዬንም ይፈጽም ዘንድና የምሻውን ያደርግ ዘንድ ንጉሡ ደስ ቢያሰኘው፥ ንጉሡና ሐማ ወደማዘጋጅላቸው ግብዣ ይምጡ፥ እንደ ንጉሡም ነገር ነገ አደርጋለሁ አለች።
9በዚያም ቀን ሐማ ደስ ብሎት በልቡም ተደስቶ ወጣ፥ ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ያለ መነሣትና ያለ መናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቈጣ። 10ሐማ ግን ታግሦ ወደ ቤቱ ሄደ፥ ልኮም ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠራ። 11ሐማም የሀብቱን ክብርና የልጆቹን ብዛት፥ ንጉሡም ያከበረበትን ክብር ሁሉ፥ በንጉሡም አዛውንትና ባሪያዎች ላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው አጫወታቸው። 12ሐማም፦ ንግሥቲቱ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር ማንንም አልጠራችም፥ ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ። 13ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንምን አይጠቅምም አለ። 14ሚስቱም ዞሳራና ወዳጆቹ ሁሉ፦ ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ ይደረግ፥ ነገም መርዶክዮስ ይሰቀልበት ዘንድ ለንጉሡ ተናገር፥ ደስም ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ግባ አሉት። ነገራቸውም ሐማን ደስ አሰኘው፥ ግንዱንም አስደረገ።
Currently Selected:
መጽሐፈ አስቴር 5: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ