ኦሪት ዘዳግም 29
29
1እግዚአብሔር በኮሬብ ካደረገው ቃል ኪዳን ሌላ በሞዓብ ምድር ከእስራኤል ልጆች ጋር ያደርገው ዘንድ ሙሴን ያዘዘው የቃል ኪዳኑ ቃሎች እነዚህ ናቸው። 2ሙሴም የእስራኤልን ልጆች ሁሉ ጠርቶ አላቸው፦ እግዚአብሔር በፊታችሁ በግብፅ ምድር በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሁሉ ያደረገውን ሁሉ፥ 3ዓይኖቻችሁ ያዩአቸውን ታላላቆች ፈተናዎች፥ ታላላቆች ተአምራትና ድንቆች፥ አይታችኋል፤ 4እግዚአብሔር ግን አስተዋይ ልብ፥ የሚያዩ ዓይኖች፥ የሚሰሙም ጆሮች እስከ ዛሬ ድረስ አልሰጣችሁም። 5አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራኋችሁ፤ ልብሳችሁም አላረጀባችሁም፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ላይ አላረጀም። 6እኔ አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ እንጀራ አልበላችሁም፥ የወይን ጠጅና የሚያሰክረውን መጠጥ አልጠጣችሁም። 7ወደዚህም ስፍራ በመጣችሁ ጊዜ የሐሴቦን ንጉሥ ሴዎን የባሳንም ንጉስ ዐግ ሊወጉን ወጡብን፥ እኛም መታናቸው፤ 8ምድራቸውንም ወስደን ለሮቤልና ለጋድ ለምናሴም ነገድ እኩሌታ ርስት አድርገን ሰጠናቸው። 9ስለዚህ በምታደርጉት ሁሉ ትከናወኑ ዘንድ የዚህን ቃል ኪዳን ቃሎች ጠብቁ አድርጉም። 10-11ሁላችሁ፥ አለቆቻችሁም ነገዶቻችሁም ሽማግሌዎቻችሁም ሹማምቶቻችሁም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ልጆቻችሁም ሴቶቻችሁም በሰፈራችሁም ያለ እንጨትህን የሚቆርጥ ውኃህንም የሚቀዳ መጻተኛ፥ ዛሬ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቆማችኋል፤ 12-13ይኸውም ዛሬ ለእርሱ ሕዝብ አድርጎ ያስነሣህ ዘንድ፥ እርሱም ለአንተ እንደ ተናገረ ለአባቶችህም ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እንደ ማለ አምላክ ይሆንልህ ዘንድ፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ዛሬ በሚያደርገው ቃል ኪዳን ትገባ ዘንድና የአምላክህን የእግዚአብሔርን መሐላ ትሰማ ዘንድ ነው። 14እኔም ይህን ቃል ኪዳንና ይህን መሐላ የማደርገው ከእናንተ ጋር ብቻ አይደለም፤ 15ነገር ግን ዛሬ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት ከእኛ ጋር በዚህ ከሚቆም ሰው ጋር፥ ዛሬም ከእኛ ጋር በዚህ ከሌለ ሰው ጋር ነው እንጂ፤ 16ነገር ግን እኛ በግብፅ ምድር እንደ ተቀመጥን በመካከላቸውም ባለፋችሁባቸው አሕዛብ መካከል እንዳለፍን አውቃችኋልና፥ 17ርኩስነታቸውንም በእነርሱም ዘንድ የነበሩትን የእንጨትና የድንጋይ የብርና የወርቅም ጣዖቶቻቸውን አይታችኋልና፥ 18ሄዶ የእነዚያን አሕዛብ አማልክት ያመልክ ዘንድ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ልቡን ዛሬ የሚያስት ወንድ ወይም ሴት ወይም ወገን ወይም ነገድ አይኑርባችሁ፤ ሐሞትና እሬትም የሚያበቅል ሥር አይሁንባችሁ። 19የዚህንም እርግማን ቃሎች የሰማ ሰው፦ ምንም እንኳ በልቤ ደንዳንነት ብሄድ፥ ለጥማቴም ስካር ብጨምር ሰላም ይሆንልኛል ብሎ ሰውነቱን በልቡ የሚባርክ ቢኖር፥ 20የእግዚአብሔር ቁጣ ቅንዓቱም በዚያ ሰው ላይ ይጤሳል እንጂ እግዚአብሔር ይቅርታ አያደርግለትም፤ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈው እርግማን ሁሉ በላዩ ይኖራል፥ እግዚአብሔርም ስሙን ከሰማይ በታች ይደመስሰዋል። 21እግዚአብሔርም በዚህ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው እንደ ቃል ኪዳኑ እርግማን ሁሉ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ ለጥፋት ይለየዋል። 22ከዚያም በኋላ የሚነሣ ትውልድ ከእናንተም በኋላ የሚሆኑ ልጆቻችሁ ከሩቅ አገርም የሚመጣ እንግዳ፥ የዚህን አገር መቅሠፍት፥ እግዚአብሔርም በእርስዋ ያደረገውን ሥቃይዋን፥ 23ምድርም በሁለንተናዋ ዲንና ጨው መቃጠልም እንደ ሆነባት፥ እንዳትዘራም እንዳታበቅልም፥ ማናቸውም ሣርና ልምላሜም እንዳይወጣባት፥ እግዚአብሔር በቁጣውና በመዓቱ እንደ ገለባበጣቸው እንደ ሰዶምና ገሞራ እንደ አዳማና እንደ ሲባዮ እንደ ሆነች ባዩ ጊዜ፥ 24አሕዛብ ሁሉ፦ እግዚአብሔር በዚህች ምድር ስለ ምን እንደዚህ አደረገ? ይህስ የቁጣው ታላቅ መቅሠፍት ምንድር ነው? ይላሉ። 25ሰዎችም እንዲህ ይላሉ፦ የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር ባወጣቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን ስለተዉ፥ 26ሄደውም የማያውቍቸውንና ያልታዘዙትን ሌሎችን አማልክት ስላመለኩና ስለ ሰገዱላቸው፥ 27ስለዚህ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን መርገም ሁሉ ያወርድባት ዘንድ የእግዚአብሔር ቁጣ በዚህች ምድር ነደደ፤ 28ዛሬም እንዳሉ እግዚአብሔር በቁጣና በመቅሠፍት በታላቅም መዓት ከምድራቸው ነቀላቸው፥ ወደ ሌላም ምድር ጣላቸው። 29ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 29: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ