ኦሪት ዘዳግም 21
21
1አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ በሚሰጥህ ምድር የተገደለ ሰው በሜዳ ወድቆ ቢገኝ፥ 2ገዳዩም ባይታወቅ፥ ሽማግሌዎችህና ፈራጆችህ ወጥተው በተገደለው ሰው ዙሪያ እስካሉት ከተሞች ድረስ በስፍር ይለኩ፤ 3ወደ ተገደለውም ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ለሥራ ያልደረሰችውን ቀንበርም ያልተጫነባትን ጊደር ይውሰዱ፤ 4የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ጊደሪቱን ይዘው ፈሳሽ ውኃ ወዳለበት ወዳልታረሰና ዘርም ወዳልተዘራበት ሸለቆ ይሄዳሉ፤ በዚያም በሸለቆው ውስጥ የጊደሪቱን አንገት ይሰብራሉ። 5የሌዊ ልጆች ካህናትም ይቀርባሉ፤ በፊቱ እንዲያገልግሉ፥ በስሙም እንዲባርኩ አምላክህ እግዚአብሔር መርጦአቸዋልና፥ በእነርሱም ቃል ክርክር ሁሉ ጉዳትም ሁሉ ይቈረጣልና፤ 6ወደ ተገደለው ሰው አቅራቢያ የሆነችው የከተማይቱ ሽማግሌዎች ሁሉ በሸለቆው ውስጥ አንገትዋ በተሰበረው ጊደር ላይ እጃቸውን ሲታጠቡ፦ 7እጃችን ይህን ደም አላፈሰሰችም፥ ዓይናችንም አላየችም፤ 8አቤቱ፥ የተቤዠኸውን ሕዝብህን እስራኤልን ይቅር በል፤ በሕዝብህም በእስራኤል ላይ የንጹሑን ደም በደል አትቁጠር ብለው ይናገራሉ። ስለ ደሙም ይሰረይላቸዋል። 9አንተም በእግዚአብሔር ዓይን የቀናውን ባደረግህ ጊዜ የንጹሑን ደም በደል ከመካከልህ ታርቃለህ። 10ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ፥ አምላክህም እግዚአብሔር በእጅህ አሳልፎ በሰጣቸው በማረክሃቸውም ጊዜ፥ 11በተማረኩት መካከል የተዋበች ሴት ብታይ፥ ብትመኛትም ሚስትም ልታደርጋት ብትወድድ፥ ወደ ቤትህ ታመጣታለህ፤ 12እርስዋም ራስዋን ትላጫለች፥ ጥፍርዋንም ትቈርጣለች፤ 13የተማረከችበትንም ልብስ ታወልቃለች፥ በቤትህም ተቀምጣ ስለ አባትዋና ስለ እናትዋ አንድ ወር ሙሉ ታለቅሳለች፤ ከዚያም በኋላ ትደርስባታለህ፥ ባልም ትሆናታለህ፥ እርስዋም ሚስት ትሆንልሃለች። 14ከዚያም በኋላ በእርስዋ ደስ ባይልህ አርነት አውጥተህ ወደ ወደደችው ትሰድዳታለህ፤ በዋጋ ግን አትሸጣትም፤ እፍረት አድርገህባታልና እንደ ባሪያ አትቈጥራትም። 15ለአንድ ሰው አንዲቱ የተወደደች አንዲቱም የተጠላች ሁለት ሚስቶች ቢኖሩት፥ ለእርሱም የተወደደችው ደግሞም የተጠላችው ልጆችን ቢወልዱ፥ በኩሩም ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ ቢሆን፥ 16ለልጆቹ ከብቱን በሚያወርስበት ቀን ከተጠላችው ሚስት በተወለደው በበኩሩ ፊት ከተወደደችው ሚስት የተወለደውን ልጅ በኩር ያደርገው ዘንድ አይገባውም፤ 17ነገር ግን ከከብቱ ሁለት እጥፍ ለእርሱ በመስጠት ከተጠላችው ሚስት የተወለደው ልጅ በኩር እንደ ሆነ ያስታውቅ። የኃይሉ መጀመሪያ ነውና በኩርነቱ የእርሱ ነው። 18ማንም ሰው ለአባቱ ቃልና ለእናቱ ቃል የማይታዘዝ ቢቀጡትም የማይሰማቸው እልከኛና ዓመፀኛ ልጅ ቢኖረው፥ 19አባቱና እናቱ ይዘው ወደ ከተማው ሽማግሌዎች ወደሚኖሩበትም ስፍራ በር ያምጡት፤ 20የከተማውንም ሽማግሌዎች፦ ይህ ልጃችን እልከኛና ዓመፀኛ ነው፥ ለቃላችንም አይታዘዝም ስስታምና ሰካራም ነው ይበሉአቸው። 21የከተማውም ሰዎች ሁሉ እስኪሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩት፤ እንዲህም ክፉውን ነገር ከመካከል ታርቃለህ፥ እስራኤልም ሁሉ ሰምተው ይፈራሉ። 22ማንም ሰው ለሞት የሚያበቃውን ኃጢአት ቢሠራ፥ እንዲሞትም ቢፈረድበት፥ በእንጨትም ላይ ብትሰቅለው፥ 23በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነውና ሬሳው በእንጨት ላይ አይደር፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ርስት አድርጎ የሰጠህን ምድር እንዳታረክስ በእርግጥ በዚያው ቀን ቅበረው።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 21: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ