የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዳንኤል 8

8
1በመጀመሪያ ከተገለጠልኝ ራእይ በኋላ፥ ንጉሡ ብልጣሶር በነገሠ በሦስተኛው ዓመት፥ ለእኔ ለዳንኤል ራእይ ተገለጠልኝ። 2በራእዩም አየሁ፥ ባየሁም ጊዜ በኤላም አውራጃ ባለው በሱሳ ግንብ ነበርሁ፥ በራእዩም አየሁ በኡባል ወንዝም አጠገብ ነበርሁ። 3ዓይኔን አንሥቼ አየሁ፥ እነሆም፥ ሁለት ቀንዶች የነበሩት አንድ አውራ በግ በወንዙ ፊት ቆሞ ነበር፥ ሁለቱም ቀንዶቹ ከፍ ከፍ ይሉ ነበር፥ አንዱ ግን ከሁለተኛው ከፍ ያለ ነበረ፥ ታላቁም ወደ ኋላው ወጥቶ ነበር። 4አውራውም በግ ወደ ምዕራብ ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም በቀንዱ ሲጐሽም አየሁ፥ አራዊትም ሁሉ ይቋቋሙት ዘንድ አልቻሉም፥ ከእጁም የሚያድን አልነበረም፥ እንደ ፈቃዱም አደረገ፥ ራሱንም ታላቅ አደረገ።
5እኔም ስመለከት፥ እነሆ፥ ከምዕራብ ወገን አንድ አውራ ፍየል በምድር ሁሉ ፊት ላይ ወጣ፥ ምድርንም አልነካም፥ ለፍየሉም በዓይኖቹ መካከል አንድ ታላቅ ቀንድ ነበረው። 6ሁለትም ቀንድ ወዳለው በወንዝም ፊት ቆሞ ወዳየሁት አውራ በግ መጣ፥ በኃይሉም ቍጣ ፈጥኖ ወደ እርሱ ሮጠ። 7ወደ አውራውም በግ ሲቀርብ አየሁት፥ እርሱም ተመረረበት፥ አውራውንም በግ መታ፥ ሁለቱንም ቀንዶች ሰበረ፥ አውራውም በግ ሊቋቋመው ኃይል አልነበረውም፥ እርሱም በምድር ላይ ጥሎ ረገጠው፥ አውራውንም በግ ከእጁ ያድነው ዘንድ የሚችል አልነበረም። 8አውራውም ፍየል ራሱን እጅግ ታላቅ አደረገ፥ በበረታም ጊዜ ታላቁ ቀንዱ ተሰበረ፥ ወደ አራቱም የሰማይ ነፋሳት የሚመለከቱ አራት ቀንዶች ከበታቹ ወጡ።
9ከእነርሱም ከአንደኛው አንድ ታናሽ ቀንድ ወጣ፥ ወደ ደቡብም ወደ ምሥራቅም ወደ መልካሚቱም ምድር እጅግ ከፍ አለ። 10እስከ ሰማይም ሠራዊት ድረስ ከፍ አለ፥ ከሠራዊትና ከከዋክብትም አያሌዎችን ወደ ምድር ጣለ፥ ረገጣቸውም። 11እስከ ሠራዊትም አለቃ ድረስ ራሱን ታላቅ አደረገ፥ ከእርሱም የተነሣ የዘወትሩ መሥዋዕት ተሻረ፥ የመቅደሱም ስፍራ ፈረሰ። 12ሠራዊቱም ከኃጢአት የተነሣ ከዘወትሩ መሥዋዕት ጋር ተሰጠው፥ እርሱም እውነትን ወደ ምድሩ ጣለ፥ አደረገም ተከናወነም። 13ከቅዱሳኑም አንዱ ሲናገር ሰማሁ፥ ለተናገረው ለቅዱሱም ሁለተኛው ቅዱስ፦ ስለ ዘወትሩ መሥዋዕት፥ መቅደሱና ሠራዊቱም ይረገጡ ዘንድ ስለሚሰጥና ስለሚያጠፋ ኃጢአት የሆነው ራእይ እስከ መቼ ይሆናል? አለው። 14እርሱም፦ እስከ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጥዋት ድረስ ነው፥ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነጻል አለኝ።
15እኔም ዳንኤል ራእዩን ባየሁ ጊዜ ማስተዋሉን ፈለግሁ፥ እነሆም፥ የሰው ምስያ በፊቴ ቆሞ ነበር። 16በኡባልም ወንዝ መካከል፦ ገብርኤል ሆይ፥ ራእዩን ለዚህ ሰው አስታውቀው ብሎ የሚጮኸውን የሰውን ድምፅ ሰማሁ። 17እኔም ወደ ቆምሁበት ቀረበ፥ በመጣም ጊዜ ፈርቼ በግምባሬ ተደፋሁ፥ እርሱም፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ ራእዩ ለፍጻሜ ዘመን እንደ ሆነ አስተውል አለኝ። 18ሲናገረኝም ደንግጬ በምድር ላይ በግምባሬ ተደፋሁ፥ እርሱም ዳሰሰኝ ቀጥ አድርጎም አቆመኝ። 19እንዲህም አለኝ፦ እነሆ፥ በመቅሠፍቱ በመጨረሻ ዘመን የሚሆነውን አስታውቅሃለሁ፥ ይህ ለተወሰነው ለፍጻሜ ዘመን ነውና። 20ባየኸው በአውራው በግ ላይ የነበሩ ሁለቱ ቀንዶች እነርሱ የሜዶንና የፋርስ ነገሥታት ናቸው። 21አውራውም ፍየል የግሪክ ንጉሥ ነው፥ በዓይኖቹም መካከል ያለው ታላቁ ቀንድ መጀመሪያው ንጉሥ ነው። 22እርሱም በተሰበረ ጊዜ በእርሱ ፋንታ አራቱ እንደ ተነሡ፥ እንዲሁ ከወገኑ አራት መንግሥታት ይነሣሉ፥ ነገር ግን በኃይል አይተካከሉትም። 23በመንግሥታቸውም መጨረሻ፥ ኃጢአታቸው በተሞላች ጊዜ፥ እንቈቅልሽን የሚያስተውል ፊተ ጨካኝ ንጉሥ ይነሣል። 24ኃይሉም ይበረታል፥ ነገር ግን በራሱ ኃይል አይደለም፥ በድንቅም ያጠፋል፥ ያደርግማል፥ ይከናወንማል፥ ኃያላንንና የቅዱሳንን ሕዝብ ያጠፋል። 25በመታለሉ ተንኰልን በእጁ ያከናውናል፥ በልቡም ይታበያል፥ ታምነውም የሚኖሩትን ብዙዎችን ያጠፋል፥ በአለቆቹም አለቃ ላይ ይቋቋማል፥ ያለ እጅም ይሰበራል። 26የተነገረውም የማታውና የጥዋቱ ራእይ እውነተኛ ነው፥ ነገር ግን ከብዙ ዘመን በኋላ ስለሚሆን ራእዩን ዝጋ። 27እኔም ዳንኤል ተኛሁ፥ አያሌም ቀን ታመምሁ፥ ከዚያም በኋላ ተነሥቼ የንጉሡን ሥራ እሠራ ነበር፥ ስለ ራእዩም አደንቅ ነበር፥ የሚያስተውለው ግን አልነበረም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ