ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:19-29

ወደ ቆላስይስ ሰዎች 1:19-29 አማ54

እግዚአብሔር ሙላቱ ሁሉ በእርሱ እንዲኖር፥ በእርሱም በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና። እናንተንም ነውርና ነቀፋ የሌላችሁና ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ያቀርባችሁ ዘንድ፥ በፊት የተለያችሁትን ክፉ ሥራችሁንም በማድረግ በአሳባችሁ ጠላቶች የነበራችሁትን አሁን በሥጋው ሰውነት በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ። ይህም፥ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል፤ ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው፥ እኔም ጳውሎስ የእርሱ አገልጋይ ሆንሁ። አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፥ ስለ አካሉም ማለት ስለ ቤተ ክርስቲያን በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጐደለውን እፈጽማለሁ። ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ፤ ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው፥ አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል፤ ለእነርሱም እግዚአብሔር በአሕዛብ ዘንድ ያለው የዚህ ምሥጢር ክብር ባለ ጠግነት ምን እንደ ሆነ ሊያስታውቅ ወደደ፥ ምሥጢሩም የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ በእናንተ ዘንድ መሆኑ ነው። እኛም በክርስቶስ ፍጹም የሚሆን ሰውን ሁሉ እናቀርብ ዘንድ ሰውን ሁሉ እየገሠጽን ሰውንም ሁሉ በጥበብ ሁሉ እያስተማርን የምንሰብከው እርሱ ነው፤ ለዚህም ነገር ደግሞ፥ በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፥ እደክማለሁ።