የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ አሞጽ 6

6
1በጽዮን ላሉ ዓለመኞች፥ በሰማርያም ተራራ ላይ ተዘልለው ለተቀመጡ፥ የእስራኤልም ቤት ወደ እነርሱ ለመጡባቸው ለአሕዛብ አለቆች ወዮላቸው! 2ወደ ካልኔ አልፋችሁ ተመልከቱ፥ ከዚያም ወደ ታላቂቱ ሐማት ሂዱ፥ ከዚያም ወደ ፍልስጥኤም ጌት ውረዱ፥ እነርሱ ከእነዚህ መንግሥታት ይሻላሉን? ወይስ ድንበራቸው ከድንበራችሁ ይሰፋልን? 3ክፉውን ቀን ከእናንተ ለምታርቁ፥ የግፍንም ወንበር ለምታቀርቡ፥ 4ከዝሆን ጥርስ በተሠራ አልጋ ላይ ለምትተኙ፥ በምንጣፋችሁም ላይ ተደላድላችሁ ለምትቀመጡ፥ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለምትበሉ፥ 5በመሰንቆም ድምፅ ለምትንጫጩ፥ እንደ ዳዊትም የዜማን ዕቃ ለምታዘጋጁ፥ 6በፋጋ የወይን ጠጅ ለምትጠጡ፥ እጅግ ባማረ ሽቱም ለምትቀቡ፥ ስለ ዮሴፍ መከራ ግን ለማታዝኑ ለእናንተ ወዮላችሁ!
7ስለዚህ በምርኮ መጀመሪያ ይማረካሉ፥ ተደላድለው ከተቀመጡትም ዘንድ ዘፈን ይርቃል። 8ጌታ እግዚአብሔር፦ የያዕቆብን ትዕቢት ተጸይፌአለሁ፥ አዳራሾቹንም ጠልቻለሁ፥ ስለዚህ ከተማይቱንና የሚኖርባትን ሁሉ አሳልፌ እሰጣለሁ ብሎ በራሱ ምሎአል፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር። 9እንዲህም ይሆናል፥ አሥር ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ ቢቀሩ እነርሱ ይሞታሉ። 10አጥንቱንም ከቤቱ ያወጡ ዘንድ የሰው ዘመድና አቃጣዩ ባነሡት ጊዜ፥ በቤቱም ውስጥ ያለውን፦ እስከ አሁን ድረስ ገና ሰው በአንተ ዘንድ አለን? ባለው ጊዜ፥ እርሱም፦ ማንም የለም ባለ ጊዜ፥ ያን ጊዜ፦ የእግዚአብሔርን ስም እንጠራ ዘንድ አይገባንምና ዝም በል ይለዋል። 11እነሆም፥ እግዚአብሔር ያዝዛል፥ ታላቁንም ቤት በማፍረስ፥ ታናሹንም ቤት በመሰባበር ይመታል። 12-13ፍርድን ወደ ሐሞት፥ የጽድቅንም ፍሬ ወደ እሬት የለወጣችሁ፥ በከንቱም ነገር ደስ የሚላችሁ፦ በኃይላችን ቀንድ የወሰድን አይደለምን? የምትሉ፥ እናንተ ሆይ፥ በውኑ ፈረሶች በጭንጫ ላይ ይጋልባሉን? ወይስ በሬዎች በዚያ ላይ ያርሳሉን? 14የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እነሆ፥ እኔ ሕዝብን አስነሣባችኋለሁ፥ ይላል የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር፥ እነርሱም ከሐማት መግቢያ ጀምረው እስከ ዓረባ ወንዝ ድረስ ያስጨንቋችኋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ