ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8
8
1ከዚህም በኋላ ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን መታ፥ አዋረዳቸውም፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ ሜቴግ አማ የተባለችውን ከተማ ወሰደ።
2ሞዓብን መታ፥ ሞዓባውያንንም በምድር ጥሎ በገመድ ሰፈራቸው፥ በሁለትም ገመድ ለሞት፥ በአንድም ገመድ ሙሉ ለሕይወት ሰፈራቸው፥ ሞዓባውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት።
3ዳዊትም ደግሞ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የነበረውን ግዛት መልሶ ለመያዝ በሄደ ጊዜ የረአብን ልጅ የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን መታ። 4ዳዊትም ከእርሱ ሺህ ሰባት መቶ ፈረሰኞች፥ ሀያ ሺህም እግረኞች ያዘ፥ ዳዊትም የሰረገለኛውን ፈረስ ሁሉ ቋንጃ ቈረጠ፥ ለመቶ ሰረገላ ብቻ አስቀረ። 5ከደማስቆም ሶርያውያን የሱባን ንጉሥ አድርአዛርን ሊረዱ በመጡ ጊዜ ዳዊት ከሶርያውን ሀያ ሁለት ሺህ ሰዎች ገደለ። 6ዳዊትም በደማስቆ ሶርያ ጭፍሮች አኖረ፥ ሶርያውያንም ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ ግብርም አመጡለት፥ እግዚአብሔርም ዳዊት በሄደበት ሁሉ ድልን ሰጠው። 7ዳዊትም ለአድርአዛር ባሪያዎች የነበሩትን የወርቅ ጋሾች ወሰደ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ይዞአቸው መጣ። 8ንጉሡም ዳዊት ከአድርአዛር ከተሞች ከቤጣሕና ከቤሮታይ እጅግ ብዙ ናስ ወሰደ።
9የሐማትም ንጉሥ ቶዑ ዳዊት የአድርአዛርን ጭፍራ ሁሉ እንደ መታ ሰማ። 10ቶዑም ከአድርአዛር ጋር ሁልጊዜ ይዋጋ ነበርና ዳዊት አድርአዛርን ድል ስለ መታ ቶዑ ልጁን አዶራምን ደኅንነቱን ይጠይቅ ዘንድ፥ ይመርቀውም ዘንድ ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፥ እርሱም የብርና የወርቅ የናስም ዕቃ ይዞ መጣ። 11-12ንጉሥ ዳዊትም ካሸነፋቸው ከአሕዛብ ሁሉ ከሶርያ ከሞዓብም ከአሞንም ልጆች ከፍልስጥኤማውያንም ከአማሌቅም ከረአብም ልጅ ከሱባ ንጉሥ ከአድርአዛር ምርኮ ከቀደሰው ብርና ወርቅ ጋር እነዚህን ደግሞ ለእግዚአብሔር ቀደሰ።
13ዳዊትም በተመለሰ ጊዜ ከኤዶምያስ አሥራ ስምንት ሺህ ሰዎች በጨው ሸለቆ ውስጥ በመምታቱ ስሙ ተጠራ። 14በኤዶምያስ ሁሉ ጭፍሮች አኖረ፥ ኤዶማውያንም ሁሉ ለዳዊት ገባሮች ሆኑ፥ እግዚአብሔርም ዳዊት በሚሄድበት ሁሉ ድልን ሰጠው።
15ዳዊትም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነገሠ፥ ዳዊትም ለሕዝቡ ሁሉ ፍርድንና ጽድቅን አደረገላቸው። 16የጽሩያ ልጅ ኢዮአብም የሠራዊት አለቃ ነበረ፥ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ፥ 17የአኪጦብም ልጅ ሳዶቅ፥ የአቢሜሌክም ልጅ አብያታር ካህናት ነበሩ፥ ሠራያም ጸሐፊ ነበረ፥ 18የዮዳሄ ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፥ የዳዊትም ልጆች አማካሪዎች ነበሩ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ