የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 5

5
1የእስራኤልም ነገድ ሁሉ ወደ ኬብሮን ወደ ዳዊት መጥተው፦ እነሆ፥ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ የሥጋህ ቁራጭ ነን። 2አስቀድሞ ሳኦል በእኛ ላይ ንጉሥ ሆኖ ሳለ እስራኤልን የምታወጣና የምታገባ አንተ ነበርህ፥ እግዚአብሔርም፦ አንተ ሕዝቤን እስራኤልን ትጠብቃለህ፥ በእስራኤልም ላይ አለቃ ትሆናለህ ብሎህ ነበር አሉት። 3የእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ ንጉሡ ወደ ኬብሮን መጡ፥ ንጉሡ ዳዊትም በኬብሮን በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን ከእርሱ ጋር አደረገ፥ በእስራኤልም ንጉሥ ይሆን ዘንድ ዳዊትን ቀቡት። 4ዳዊትም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ዓመት ልጅ ነበረ፥ አርባ ዓመትም ነገሠ። 5በኬብሮን በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነገሠ፥ በኢየሩሳሌምም በእስራኤል ሁሉና በይሁዳ ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።
6ንጉሡና ሰዎቹም በአገሩ ውስጥ ከተቀመጡት ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት ወደ ኢየሩሳሌም ሄዱ፥ እነርሱም፦ ዳዊት ወደዚህ ሊገባ አይችልም ብለው አስበው ነበርና ዳዊትን፦ ዕውሮችንና አንካሶችን ካላወጣህ በቀር ወደዚህ አትገባም አሉት። 7ነገር ግን ዳዊት አምባይቱን ጽዮንን ያዘ፥ እርስዋም የዳዊት ከተማ ናት። 8በዚያም ቀን ዳዊት፦ ኢያቡሳውያንን የሚመታ በውኃ መሄጃው ይውጣ፥ የዳዊትም ነፍስ የምትጠላቸውን ዕውሮችንና አንካሶችን ያውጣ አለ። ስለዚህም በምሳሌ፦ ዕውርና አንካሳ ወደ ቤት አይግቡ ተባለ። 9ዳዊትም በአምባይቱ ውስጥ ተቀመጠ፥ የዳዊትም ከተማ ብሎ ጠራት። ዳዊትም ዙሪያዋን ከሚሎ ጀምሮ ወደ ውስጥ ቀጠራት። 10ዳዊትም እየበረታ ሄደ፥ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ።
11የጢሮስም ንጉሥ ኪራም ወደ ዳዊት መልእክተኞችን የዝግባ እንጨትንም አናጢዎችንም ጠራቢዎችንም ላከ፥ ለዳዊትም ቤት ሠሩለት። 12ዳዊትም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናው፥ ስለ ሕዝቡ ስለ እስራኤልም መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገ አወቀ።
13ዳዊትም ከኬብሮን ከመጣ በኋላ ሌሎቹን ቁባቶቹንና ሚስቶቹን ከኢየሩሳሌም ወሰደ፥ ለዳዊትም ደግሞ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ተወለዱለት። 14በኢየሩሳሌምም የተወለዱለት ስማቸው ይህ ነው፥ ሳሙስ፥ 15ሶባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥ ኢያቤሐር፥ ኤሊሱዔ፥ 16ናፌቅ፥ ያፍያ፥ ኤሊሳማ፥ ኤሊዳሄ፥ ኤሊፋላት።
17ፍልስጥኤማውያንም ዳዊት በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆኖ እንደ ተቀባ ሰሙ፥ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ዳዊትን ሊፈልጉ ወጡ፥ ዳዊትም በሰማ ጊዜ ወደ ምሽጉ ወረደ። 18ፍልስጥኤማውያንም መጥተው በራፋይም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ። 19ዳዊትም፦ ወደ ፍልስጥኤማውያን ልውጣን? በእጄስ አሳልፈህ ትሰጣቸዋለህን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም ዳዊትን፦ ፍልስጥኤማውያንን በእርግጥ በእጅህ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁና ውጣ አለው። 20ዳዊትም ወደ በኣልፐራሲም መጣ፥ በዚያም መታቸውና፦ ውኃ እንዲያፈርስ እግዚአብሔር ጠላቶቼን በፊቴ አፈረሳቸው አለ። ስለዚህም የዚያን ስፍራ ስም በኣልፐራሲም ብሎ ጠራው። 21ጣዖቶቻቸውንም በዚያ ተዉ፥ ዳዊትና ሰዎቹም ወሰዱአቸው።
22ፍልስጥኤማውያንም ደግሞ መጡ፥ በራፋይምም ሸለቆ ተበትነው ሰፈሩ። 23ዳዊትም እግዚአብሔርን ጠየቀ፥ እርሱም፦ በኋላቸው ዞረህ በሾላው ዛፍ ፊት ለፊት ግጠማቸው እንጂ አትውጣ። 24በሾላውም ዛፍ ራስ ውስጥ የሽውሽውታ ድምፅ ስትሰማ፥ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ለመምታት በፊትህ ወጥቶ ይሆናልና በዚያን ጊዜ ቸኩል አለው። 25ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፥ ከገባዖንም እስከ ጌዝር ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ