ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 24

24
1ደግሞም የእግዚአብሔር ቍጣ በእስራኤል ላይ ነደደ፥ ዳዊትም፦ ሂድ፥ እስራኤልንና ይሁዳን ቍጠር ብሎ በላያቸው አስነሣው። 2ንጉሡም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሠራዊት አለቆች፦ የሕዝቡን ድምር አውቅ ዘንድ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ተመላለሱ፥ ሕዝቡንም ቍጠሩአቸው አላቸው። 3ኢዮአብም ንጉሡን፦ የጌታዬ የንጉሡ ዓይን እያየ አምላክህ እግዚአብሔር ዛሬ ካለው ሕዝብ መጠን በላይ መቶ እጥፍ ይጨምርበት፥ ጌታዬ ንጉሡ ግን ይህን ነገር ለምን ይወድዳል? አለው። 4ነገር ግን የንጉሡ ቃል በኢዮአብና በሠራዊቱ አለቆች ላይ አሸነፈ። ኢዮአብና የሠራዊቱ አለቆችም የእስራኤልን ሕዝብ ይቆጥሩ ዘንድ ከንጉሥ ዘንድ ወጡ። 5ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ በጋድ ሸለቆ መካከል ባለችው በኢያዜር ከተማ ቀኝ በኩል በአሮዔር ላይ ሰፈሩ። 6ወደ ገለዓድም ወደ ተባሶን አዳሰይ አገር መጡ፥ ወደ ዳንየዓንም ደረሱ፥ ወደ ሲዶናም ዞሩ፥ 7ወደ ጢሮስም ምሽግ ወደ ኤዊያውያንና ወደ ከነዓናውያንም ከተሞች ሁሉ መጡ፥ በይሁዳም ደቡብ በኩል በቤርሳቤህ ወጡ። 8በአገሪቱም ሁሉ ላይ ተመላልሰው ከዘጠኝ ወርና ከሀያ ቀን በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 9ኢዮአብም የሕዝቡን ቍጥር ድምር ለንጉሡ ሰጠ፥ በእስራኤልም ሰይፍ የሚመዝዙ ስምንት መቶ ሺህ ጽኑዓን ሰዎች ነበሩ፥ የይሁዳም ሰዎች አምስት መቶ ሺህ ነበሩ።
10ሕዝቡንም ከቈጠረ በኋላ ዳዊትን ልቡ መታው፥ ዳዊትም እግዚአብሔርን፦ ባደረግሁት ነገር እጅግ በድያለሁ፥ አሁን ግን፥ አቤቱ፥ ታላቅ ስንፍና አድርጌአለሁና የባሪያህን ኃጢአት ታርቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው። 11ዳዊትም ማልዶ በተነሣ ጊዜ፥ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ዳዊት ባለ ራእይ ወደ ነቢዩ ወደ ጋድ እንዲህ ሲል መጣ፦ 12ሂድ ለዳዊት፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሦስት ነገሮች በፊትህ አኖራለሁ፥ አደርግብህ ዘንድ ከእነርሱ አንዱን ምረጥ ብለህ ንገረው አለው። 13ጋድም ወደ ዳዊት መጥቶ፦ የሦስት ዓመት ራብ በአገርህ ላይ ይምጣብህን? ወይስ ጠላቶችህ እያሳደዱህ ሦስት ወር ከእነርሱ ትሸሽን? ወይስ የሦስት ቀን ቸነፈር በአገርህ ላይ ይሁን? አሁንም ለላከኝ ምን መልስ እንደምሰጥ አስብና መርምር ብሎ ነገረው። 14ዳዊትም ጋድን፦ እጅግ ተጨንቄአለሁ፥ ምሕረቱ ብዙ ነውና በእግዚአብሔር እጅ እንውደቅ፥ በሰው እጅ ግን አልውደቅ አለው።
15ዳዊትም ቸነፈሩን መረጠ፥ የስንዴም መከር ወራት በሆነ ጊዜ ቸነፈሩ በሕዝቡ መካከል ጀመረ፥ ከሕዝቡም ሰባ ሺህ ሰው ሞተ። 16የእግዚአብሔርም መልአክ ኢየሩሳሌምን ያጠፋት ዘንድ እጁን በዘረጋ ጊዜ እግዚአብሔር ስለ ክፉው ነገር አዘነ፥ ሕዝቡንም የሚያጠፋውን መልአክ፦ እንግዲህ በቃህ፥ እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ነበረ። 17ዳዊትም ሕዝቡን የሚመታውን መልአክ ባየ ጊዜ እግዚአብሔርን፦ እነሆ፥ እኔ በድያለሁ ጠማማም ሥራ እኔ አድርጌአለሁ፥ እነዚህ በጎች ግን እነርሱ ምን አደረጉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን እለምንሃለሁ ብሎ ተናገረው።
18በዚያም ቀን ጋድ ወደ ዳዊት መጥቶ፦ ውጣ፥ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ አለው። 19ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንደ ጋድ ነገር ወጣ። 20ኦርናም ሲመለከት ንጉሡና ባሪያዎቹ ወደ እርሱ ሲመጡ አየ፥ ኦርናም ወጥቶ በንጉሡ ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ተደፋ። 21ኦርናም፦ ጌታዬን ንጉሡን ወደ ባሪያው ያመጣው ምክንያት ምንድር ነው? አለ። ዳዊትም፦ መቅሠፍቱ ከሕዝቡ ላይ ይከለከል ዘንድ አውድማውን ከአንተ ገዝቼ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ልሠራ ነው አለው። 22ኦርናም ዳዊትን፦ ጌታዬ ንጉሡ እንደ ወደደ ወስዶ ያቅርብ፥ እነሆ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት በሬዎች፥ ለሚቃጠልም እንጨት የአውድማ ዕቃና የበሬ ቀንበር አለ። 23ንጉሥ ሆይ፥ ይህን ሁሉ ኦርና ለንጉሡ ይሰጣል አለው፥ ኦርናም ንጉሡን፦ አምላክህ እግዚአብሔር ይቀበልህ አለው። 24ንጉሡም ኦርናን፦ እንዲህ አይደለም፥ ነገር ግን በዋጋ ከአንተ እገዛለሁ፥ ለአምላኬም ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ያለዋጋ አላቀርብም አለው። ዳዊትም አውድማውንና በሬዎቹን በአምሳ ሰቅል ብር ገዛ። 25በዚያም ዳዊት ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፥ የሚቃጠልና የደኅነትንም መሥዋዕት አቀረበ። እግዚአብሔርም ስለ አገሪቱ የተለመነውን ሰማ፥ መቅሠፍቱም ከእስራኤል ተከለከለ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ