ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2
2
1ከዚያም በኋላ ዳዊት፦ ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን? ብሎ እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦ ውጣ አለው። ዳዊትም፦ ወዴት ልውጣ? አለ። እርሱም፦ ወደ ኬብሮን ውጣ አለው። 2ዳዊትም ከሁለቱ ሚስቶቹ ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ ጋር ወደዚያ ወጣ። 3ዳዊትም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎችና ቤተ ሰባቸውን ሁሉ አመጣ፥ በኬብሮንም ከተሞች ተቀመጡ። 4የይሁዳም ሰዎች መጥተው በይሁዳ ቤት ይነግሥ ዘንድ ዳዊትን በዚያ ቀቡት። 5ዳዊትም ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፦ እናንተ ለጌታችሁ ለሳኦል ይህን ቸርነት አድርጋችኋልና፥ ቀብራችሁትማልና በእግዚአብሔር የተባረካችሁ ሁኑ። 6አሁንም እግዚአብሔር ቸርነትንና እውነትን ያድርግላችሁ፥ ይህንም ነገር አድርጋችኋልና እኔ ደግሞ ይህን ቸርነት እመልስላችኋለሁ። 7አሁንም ጌታችሁ ሳኦል ሞቶአልና እጃችሁ ትጽና፥ እናንተም ጨክኑ፥ ዳግም የይሁዳ ቤት በእነርሱ ላይ ንጉሥ እሆን ዘንድ ቀብተውኛል።
8የሳኦልም ጭፍራ አለቃ የኔር ልጅ አበኔር የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ መሃናይም አሻገረው፥ 9በገለዓድና በአሹራውያን በኢይዝራኤልም በኤፍሬምም በብንያምም በእስራኤልም ሁሉ ላይ አነገሠው። 10የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴም በእስራኤል ላይ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበረ፥ ሁለት ዓመትም ነገሠ፥ ነገር ግን የይሁዳ ቤት ዳዊትን ተከተለ። 11ዳዊትም በይሁዳ ቤት ነግሦ በኬብሮን የተቀመጠበት ዘመን ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።
12የኔር ልጅ አበኔርና የሳኦል ልጅ የኢያቡስቴ ባሪያዎች ከመሃናይም ወደ ገባዖን ወጡ። 13የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ባሪያዎች ወጥተው በገባዖን ውኃ መቆሚያ አጠገብ ተገናኙአቸው፥ በውኃውም መቆሚያ በአንዱ ወገን እነዚህ፥ በሌላውም ወገን እነዚያ ሆነው ተቀመጡ። 14አበኔርም ኢዮአብን፦ ጕልማሶች ይነሡ፥ በፊታችንም ይቆራቆሱ አለው፥ ኢዮአብም፦ ይነሡ አለ። 15ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ አሥራ ሁለት፥ ከዳዊትም ባሪያዎች አሥራ ሁለት ተቆጥረው ተነሡ። 16ሁሉም እያንዳንዱ የወደረኛውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በወደረኛው ጎን ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። የዚያም ስፍራ ስም የስለታም ሰይፍ እርሻ ተብሎ ተጠራ፥ እርሱም በገባዖን ነው። 17በዚያም ቀን ጽኑ ሰልፍ ሆነ፥ በዳዊትም ባሪያዎች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ።
18በዚያም ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብና አቢሳ አሣሄልም ነበሩ፥ አሣሄልም እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ። 19አሣሄልም የአበኔርን ፍለጋ ተከታተለ፥ አበኔርንም ከማሳደድ ቀኝና ግራ አላለም። 20አበኔርም ዘወር ብሎ ተመለከተና፦ አንተ አሣሄል ነህን? አለ። እርሱም፦ እኔ ነኝ አለ። 21አበኔርም፦ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ፈቀቅ በል፥ አንድ ጕልማሳ ያዝ፥ መሣርያውንም ውስድ አለው። አሣሄል ግን እርሱን ከማሳደድ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ። 22አበኔርም አሣሄልን፦ ከምድር ጋር እንዳላጣብቅህ እኔን ከማሳደዱ ፈቀቅ በል፥ ወደ ወንድምህ ወደ ኢዮአብ ፊቴን አቅንቼ አይ ዘንድ እንዴት ይቻለኛል? አለው። 23ነገር ግን ከእርሱ ፈቀቅ ይል ዘንድ እንቢ አለ፥ አበኔርም በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በኋላው ወጣ፥ በዚያም ስፍራ ወድቆ ሞተ። አሣሄልም ወድቆ በሞተበቱ ስፍራ የሚያልፍ ሁሉ ይቆም ነበር።
24ኢዮአብና አቢሳም አበኔርን አሳደዱ፥ በገባዖንም ምድረ በዳ መንገድ በጋድ ፊት ለፊት እስካለው እስከ አማ ኮረብታ ድረስ በወጡ ጊዜ ፀሐይ ጠለቀች። 25የብንያምም ልጆች ወደ አበኔር ተሰበሰቡ፥ በአንድነትም ሆኑ፥ በኮረብታም ራስ ላይ ቆሙ። 26አበኔርም ወደ ኢዮአብ ጮኸ፦ ሰይፍ በውኑ እስከ ዘላለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደ ሆነ አታውቅምን? ሕዝቡ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ ይመለሱ ዘንድ ሕዝቡን የማትናገር እስከ መቼ ነው? አለው። 27ኢዮአብም፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ባትናገር ኖሮ ሕዝቡ በጥዋት ወጥተው በሄዱ ነበር፥ ወንድሞቻቸውንም ማሳደድ በተዉ ነበር አለ። 28ኢዮአብም ቀንደ መለከት ነፋ፥ ሕዝቡም ሁሉ ቆመ፥ ከዚያም በኋላ እስራኤልን አላሳደደም፥ ሰይፍም አላደረገም። 29አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ዓረባ እያለፉ ሄዱ፥ ዮርዳኖስንም ተሻገሩ፥ ቢትሮንንም ሁሉ ካለፉ በኋላ ወደ መሃናይም መጡ።
30ኢዮአብም አበኔርን ከማሳደድ ተመለሰ፥ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበ፥ ከዳዊትም ባሪያዎች ከአሣሄል ሌላ አሥራ ዘጠኝ ሰዎች ጐደሉ። 31የዳዊትም ባሪያዎች ከብንያምና ከአበኔር ሰዎች ሦስት መቶ ስድሳ ያህል ገደሉ። 32አሣሄልንም አንሥተው በቤተ ልሔም በአባቱ መቃብር ቀበሩት፥ ኢዮአብና ሰዎቹም ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ በኬብሮንም አነጉ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ