የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12

12
1እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፥ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፦ በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። 2ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው። 3ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፥ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፥ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች። 4ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፥ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። 5ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። 6ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው።
7ናታንም ዳዊትን አለው፦ ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፥ 8የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፥ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። 9አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፥ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። 10ስለዚህም አቃልለኽኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም። 11እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ፥ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል። 12አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል፥ እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ። 13ዳዊትም ናታንን፦ እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል፥ አትሞትም። 14ነገር ግን በዚህ ነገር ለእግዚአብሔር ጠላቶች ታላቅ የስድብ ምክንያት አድርገሃልና ስለዚህ ደግሞ የተወለደልህ ልጅ ፈጽሞ ይሞታል አለው። 15ናታንም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
እግዚአብሔርም የኦርዮ ሚስት ለዳዊት የወለደችውን ሕፃን ቀሠፈ፥ እጅግም ታምሞ ነበር። 16ዳዊትም ስለ ሕፃኑ እግዚአብሔርን ለመነ፥ ዳዊትም ጾመ፥ ገብቶም በመሬት ላይ ተኛ። 17የቤቱም ሽማግሌዎች ተነሥተው ከምድር ያነሡት ዘንድ በአጠገቡ ቆሙ፥ እርሱ ግን እንቢ አለ፥ ከእነርሱም ጋር እንጀራ አልበላም። 18በሰባተኛውም ቀን ሕፃኑ ሞተ። የዳዊትም ባሪያዎች፦ ሕፃኑ በሕይወት ሳለ ብንነግረው አልሰማንም፥ ይልቁንስ ሕፃኑ እንደ ሞተ ብንነግረው እንዴት ይሆን? በነፍሱ ክፉ ያደርጋል ብለው ሕፃኑ እንደ ሞተ ይነግሩት ዘንድ ፈሩ። 19ዳዊትም ባሪያዎቹ በሹክሹክታ ሲነጋገሩ ባየ ጊዜ ዳዊት ሕፃኑ እንደ ሞተ አወቀ፥ ዳዊትም ባሪያዎቹን፦ ሕፃኑ ሞቶአል? አላቸው። እነርሱም፦ ሞቶአል አሉት። 20ዳዊትም ከምድር ተነሥቶ ታጠበ፥ ተቀባም፥ ልብሱንም ለወጠ፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ገብቶ ሰገደ። ወደ ቤቱም መጣ፦ እንጀራ አምጡልኝ አለ፥ 21በፊቱም አቀረቡለት፥ በላም። ባሪያዎቹም፦ ይህ ያደረግኸው ነገር ምንድር ነው? በሕይወት ሳለ ስለ ሕፃኑ ጾምህና አለቀስህ፥ ከሞተ በኋላ ግን ተነሥተህ እንጀራ በላህ አሉት። 22እርሱም፦ ሕፃኑ ሕያው ሳለ፦ እግዚአብሔር ይምረኝ፥ ሕፃኑም በሕይወት ይኖር እንደ ሆነ ማን ያውቃል? ብዬ ጾምሁ አለቀስሁም። 23አሁን ግን ሞቶአል፥ የምጾመው ስለ ምንድር ነው? በውኑ እንግዲህ እመልሰው ዘንድ ይቻለኛልን? እኔ ወደ እርሱ እሄዳለሁ እንጂ እርሱ ወደ እኔ አይመለስም አለ።
24ዳዊትም ሚስቱን ቤርሳቤህን አጽናናት፥ ወደ እርስዋም ገባ፥ ከእርስዋም ጋር ተኛ፥ ወንድ ልጅም ወለደች፥ ስሙንም ሰሎሞን ብሎ ጠራው። እግዚአብሔርም ወደደው፥ 25ደግሞም በነቢዩ በናታን እጅ ልኮ ስሙን ስለ እግዚአብሔር ይዲድያ ብሎ ጠራው።
26ኢዮአብም የአሞንን ልጆች ከተማ ረባትን ወጋ፥ የውኃውንም ከተማ ያዘ። 27ኢዪአብም ወደ ዳዊት፦ ረባትን ወግቻለሁ፥ የውኃውንም ከተማ ይዤአለሁ። 28-29አሁንም ከተማይቱን እንዳልይዝ፥ በስሜም እንዳትጠራ፥ የቀረውን ሕዝብ ሰብስብ፥ ከተማይቱንም ከብበህ ያዝ ብሎ መልእክተኞችን ላከ። ዳዊትም ሕዝቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ረባት ሄደ፥ ወግቶም ያዛት። 30የንጉሣቸውንም ዘውድ ከራሱ ላይ ወሰደ። ክብደቱም አንድ መክሊት ወርቅ ያህል ነበር፥ ክቡር ዕንቁም ነበረበት፥ ዳዊትም በራሱ ላይ አደረገው። ከከተማይቱም እጅግ ብዙ ምርኮ አወጣ። 31በውስጥዋም የነበሩትን ሕዝብ አውጥቶ በመጋዝና በብረት መቆፈሪያና በብረት መጥረቢያ እንዲሠሩ አደረጋቸው፥ የሸክላ ጡብም እንዲያቃጥሉ አደረጋቸው፥ በአሞን ልጆች ከተሞች ሁሉ እንዲህ አደረገ። ዳዊትም ሕዝቡም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ