ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 11

11
የይሁዳ ንግሥት ጎቶልያ
(2ዜ.መ. 22፥10—23፥15)
1የአካዝያስም እናት ጎቶልያ ልጅዋ እንደ ሞተ ባየች ጊዜ ተነሥታ የመንግሥትን ዘር ሁሉ አጠፋች። 2የንጉሡ የኢዮራም ልጅ የአካዝያስ እኅት ዮሳቤት የአካዝያስን ልጅ ኢዮአስን ወስዳ ከተገደሉት ከንጉሥ ልጆች መካከል ሰረቀችው፤ እርሱንና ሞግዚቱንም ወደ እልፍኝ ወሰደች፤ እንዳይገደልም ከጎቶልያ ሸሸጉት። 3በእርስዋም ዘንድ ተሸሸጎ በእግዚአብሔር ቤት ስድስት ዓመት ያህል ተቀመጠ። ጎቶልያም በምድር ላይ ነገሠች።
ዮዳሄ ኢዮአስን ለንጉሥነት እንደ ቀባው
4በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ ልኮ በካራውያንና በዘበኞች ላይ ያሉትን የመቶ አለቆች ወሰደ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት አገባቸው፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ በእግዚአብሔርም ቤት አማላቸው፤ የንጉሡንም ልጅ አሳያቸው። 5እንዲህም ብሎ አዘዛቸው “እንዲህ አድርጉ፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ የንጉሡን ቤት ዘብ ጠብቁ፤ 6ከእናንተ ከሦስት አንዱ እጅ በሱር በር ሁኑ፤ አንዱም እጅ ከዘበኞች ቤት በኋላ ባለው በር ሁኑ፤ ቤቱንም ጠብቁ፤ ከልክሉም፤ 7ከእናንተም በሰንበት ቀን የምትወጡት ሁለቱ እጅ በንጉሥ ዙሪያ ሆናችሁ የእግዚአብሔርን ቤት ጠብቁ። 8ንጉሡንም በዙሪያው ክበቡት፤ የጦር ዕቃችሁም በእጃችሁ ይሁን፤ በሰልፋችሁ መካከል የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም በወጣና በገባ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሁኑ።”
9መቶ አለቆችም ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ከእነርሱም እያንዳንዱ በሰንበት ይገቡ የነበሩትን፥ በሰንበቱም ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ይዘው ወደ ካህኑ ወደ ዮዳሄ መጡ። 10ካህኑም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር ሁሉ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 11ዘበኞቹም ሁሉ እያንዳንዳቸው የጦር ዕቃቸውን በእጃቸው ይዘው በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ ቆሙ። 12የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፤ ምስክሩንም ሰጠው፤ ቀብተውም ንጉሥ አደረጉትና “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ!” እያሉ እጃቸውን አጨበጨቡ።
የጎቶልያ መሞት
13ጎቶልያም የሠራዊቱንና የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች። 14እነሆም፥ ንጉሡ እንደ ተለመደው በዓምዱ አጠገብ ቆሞ፥ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች፤ የአገሩም ሕዝብ ሁል ደስ ብሎአቸው ቀንደ መለከት ይነፉ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ “ዐመፅ ነው! ዐመፅ ነው!” ብላ ጮኸች። 15ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች “ወደ ሰልፉ መካከል አውጡአት፤ የሚከተላትንም በሰይፍ ግደሉት፤” ብሎ አዘዛቸው፤ ካህኑ “በእግዚአብሔር ቤት አትገደል፤” ብሎአልና። 16እጃቸውንም በእርስዋ ላይ ጫኑ፤ በፈረሱም መግቢያ መንገድ ወደ ንጉሥ ቤት ወሰዱአት፤ በዚያም ገደሉአት።”
17ዮዳሄም የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ በእግዚአብሔርና በንጉሡ በሕዝቡም መካከል ቃል ኪዳን አደረገ፤ ደግሞም በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ቃል ኪዳን አደረገ። 18የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በኣል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹን አደቀቁ፤ የበኣልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ካህኑም ለእግዚአብሔር ቤት አስተዳዳሪዎችን ሾመ። 19መቶ አለቆቹንና ካራውያንንም፥ ዘበኞችንና የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረዱት፤ በዘበኞችም በር መንገድ ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ በነገሥታቱም ዙፋን ተቀመጠ። 20የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፤ ከተማይቱም ጸጥ አለች። ጎቶልያንም በንጉሡ ቤት አጠገብ በሰይፍ ገደሉአት። 21ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ