ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 6
6
ሰሎሞን ለሕዝቡ የተናገረው ቃል
(1ነገ. 8፥12-21)
1ሰሎሞንም “እግዚአብሔር ‘በጨለማ ውስጥ እኖራለሁ፤’ ብሎአል፤ 2እኔ ግን ለዘላለም ትኖርበት ዘንድ ማደሪያ ቤትን ሠራሁልህ፤” አለ። 3ንጉሡም ፊቱን ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። 4እርሱም አለ “ለአባቴ ለዳዊት በአፉ የተናገረ በእጁም የፈጸመ የእስራኤል እምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤ 5እርሱ ‘ሕዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤት በዚያ ይሠራልኝ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ማንኛውንም ከተማ አልመረጥሁም፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም፤ 6ነገር ግን ስሜ በዚያ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ፤’ ብሎአልና። 7አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ በልቡ አስቦ ነበር። 8እግዚአብሔርም አባቴን ዳዊትን ‘ለስሜ ቤት ትሥራ ዘንድ በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ መልካም አደረግህ። 9ነገር ግን ከወገብህ የሚወጣው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም፤’ አለው። 10እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጸመ፤ እግዚአብሔርም ተስፋ እንደ ሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፤ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፤ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤት ሠራሁ። 11ከእስራኤልም ልጆች ጋር ያደረገው የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት በዚያው ውስጥ አኖርሁ።”
ሰሎሞን ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው ጸሎት
(1ነገ. 8፥22-53)
12-13ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መደገፊያ ሠርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፤ በላዩም ቆመ፤ በእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ፊት በጕልበቱ ተንበርክኮ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ እያዩ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹንም ዘርግቶ እንዲህ አለ 14“አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! በሰማይ ወይም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባሪያዎችህ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ፥ 15ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፥ በአፍህ ተናገርህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው። 16አሁንም፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ‘አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ በሕጌ ይሄዱ ዘንድ መንገዳቸውን ቢጠብቁ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም፤’ ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለባሪያህ ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ። 17አሁንም፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ለባሪያህ ለዳዊት የተናገረኸው ቃል ይጽና።
18“በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ ይሆን? 19ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ! ወደ ባሪያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፤ ባሪያህም በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። 20ባሪያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት ትሰማ ዘንድ ‘በዚያ ስሜ ይሆናል፤’ ወዳልኸው ስፍራ፥ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ቀንና ሌሊት የተገለጡ ይሁኑ። 21ባሪያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
22“ሰው ባልንጀራውን ቢበድል፥ በላዩም መሐላ ቢጫን፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ 23በሰማይ ስማ፤ አድርግም፤ በባሪያዎችህም ላይ ዳኛ ሁን፤ በበደለኛውም ላይ ፍረድ፤ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑንም አጽድቀው፤ እንደ ጽድቁም ክፈለው።
24“ሕዝብህም እስራኤል አንተን ስለ በደሉ በጠላት ፊት ድል ተመትተው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ በዚህም ቤት በፊትህ ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ 25አንተ በሰማይ ስማ፤ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱም ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው።
26“አንተን ስለ በደሉ ሰማያት በተዘጉ ጊዜ፥ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኀጢአታቸው ቢመለሱ፥ 27አንተ በሰማይ ስማ፤ የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኀጢአት ይቅር በል፤ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ አሳያቸው፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብን ስጥ።
28“በምድር ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ ጠላቶቻቸውም የአገሩን ከተሞች ከብበው ቢያስጨንቁአቸው፥ ማናቸውም መቅሠፍትና ደዌ ቢሆን፥ 29ማንም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ፥ ማናቸውም ሰው ሕመሙንና ኀዘኑን አውቆ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ፥ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ 30-31ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፈሩህ ዘንድ፥ በመንገዶችህም ይሄዱ ዘንድ፥ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው።
32“ከሕዝብህም ከእስራኤል ያልሆነ እንግዳ ስለ ታላቁ ስምህ ስለ ብርቱውም እጅህ ስለ ተዘረጋውም ክንድህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ 33አንተ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን ያውቁ ዘንድ፥ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል ይፈሩህ ዘንድ፥ በዚህም በሠራሁት ቤት ስምህ እንደ ተጠራ ያውቁ ዘንድ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።
34“ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለአንተ ቢጸልዩ፥ 35ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው።
36“የማይበድል ሰው የለምና አንተን ቢበድሉ፥ ተቈጥተህም ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅም ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር ቢማርኩአቸው፥ 37በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በምርኮአቸውም አገር ሳሉ ተመልሰው ‘ኀጢአት ሠርተናል፤ በድለንማል፤ ክፉም አድርገናል፤’ ብለው ቢለምኑህ፥ 38በተማረኩበትም በምርኮአቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ 39ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ፍርድንም አድርግላቸው፤ አንተንም የበደሉህን ሕዝብህን ይቅር በል።
40“አሁንም፥ አምላኬ ሆይ! በዚህ ስፍራ ወደሚሆነው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፥ ጆሮችህም የሚያደምጡ እንዲሆኑ እለምንሃለሁ። 41አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ! ከኀይልህ ታቦት ጋር ወደ ዕረፍትህ ተነሣ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ! ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በደስታ ደስ ይበላቸው። 42አቤቱ አምላክ ሆይ! የቀባኸውን ሰው ፊት አትመልስ ለባሪያም ለዳዊት ያደረግህለትን ምሕረት አስብ።”
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 6: አማ54
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ