የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4

4
የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች መሟላት
(1ነገ. 7፥23-26)
1ደግሞም ርዝመቱ ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ዐሥር ክንድ የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ። 2ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ። 3በበታቹም ለአንድ ክንድ ዐሥር፥ ለአንድም ክንድ አሥር፥ ጕብጕቦች አዞረበት፤ ኵሬውም በቀለጠ ጊዜ ጕብጕቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። 4በዐሥራ ሁለትም በሬዎችም ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ኵሬውም በላያቸው ነበረ፤ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። 5ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሩም አንድ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም የባዶስ መሥፈሪያ ይይዝ ነበር። 6ደግሞም ዐሥር የመታጠቢያ ሰኖች ሠራ፤ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኵሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር።
7ዐሥሩንም መቅረዞች እንደ ሥርዓታቸው ከወርቅ ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። 8ዐሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱን በግራ በመቅደስ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ድስቶች ሠራ። 9ደግሞም የካህናቱን አደባባይ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፤ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ። 10ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።
11ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን፥ ድስቶቹንም ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። 12ሁለቱን አዕማድ፥ ጽዋዎቹንም፥ በፃምዶቹምም ላይ የነበሩትን ሁለት ጕልላቶች፥ በዓምዶቹም ላይ የነበሩትን የጕልላቶች ሁለቱን ጽዋዎች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች ሠራ። 13በዓምዶቹም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ፥ ለእያንዳንዱ መረበብ ሁለት ሁለት ተራ ሮማኖች፥ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ። 14መቀመጫዎቹንና በመቀመጫዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሰኖች፥ 15አንዱንም ኵሬ፥ በበታቹም የሚሆኑትን ዐሥራ ሁለት በሬዎች ሠራ። 16ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም ሜንጦዎቹንም ዕቃቸውንም ሁሉ ኪራም ለንጉሡ ለሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት ከለስላሳ ናስ ሠራ። 17ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው። 18ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም ሚዛን አይቈጠርም ነበር።
19ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ፥ የወርቁንም መሠዊያ፥ የገጹንም ኅብስት የነበረባቸውን ገበታዎች፥ 20በቅድስተ ቅዱሳንም ፊት እንደ ሥርዓታቸው ያበሩ ዘንድ መቅረዞችንና ቀንዲሎቻቸውን ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 21አበባዎቹንና ቀንዲሎቹን መኮስተሪያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። 22ጕጠቶቹንም ድስቶቹንም ጭልፋዎቹንም ማንደጃዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። የውስጠኛውም ቤት የቅድስተ ቅዱሳን ደጆች የቤተ መቅደሱም ደጆች የወርቅ ነበሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ