አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 27
27
1ዳዊትም በልቡ፦ አንድ ቀን በሳኦል እጅ እጠፋለሁ ወደ ፍልስጥኤማውያንም ምድር ከመሸሽ በቀር የሚሻለኝ የለም፥ ሳኦልም በእስራኤል አውራጃ ሁሉ እኔን መሻት ይተዋል፥ እንዲህም ከእጁ እድናለሁ አለ። 2ዳዊትም ከእርሱም ጋር የነበሩት ስድስቱ መቶ ሰዎች ተነሥተው ወደ ጌት ንጉሥ ወደ አሜህ ልጅ ወደ አንኩስ አለፉ። 3ዳዊትና ሰዎቹም እያንዳንዳቸው ከነ ቤተ ሰቡ ከአንኩስ ጋር በጌት ውስጥ ተቀመጡ፥ ከዳዊትም ጋር ኢይዝራኤላዊቱ አኪናሆምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት አቢግያ ሁለቱ ሚስቶቹ ነበሩ። 4ሳኦልም ዳዊት ወደ ጌት እንደ ኮበለለ ሰማ፥ ከዚያም በኋላ ደግሞ አልፈለገውም።
5ዳዊትም አንኩስን፦ በዓይንህ ፊት ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ በዚህ አገር በአንዲቱ ከተማ የምቀመጥበት ስፍራ ስጠኝ፥ ስለ ምን እኔ ባሪያህ ከአንተ ጋር በንጉሥ ከተማ እቀመጣለሁ? አለው። 6በዚያም ቀን አንኩስ ጺቅላግን ሰጠው፥ ስለዚህም ጺቅላግ እስከ ዛሬ ድረስ ለይሁዳ ነገሥታት ሆነች። 7ዳዊትም በፍልስጥኤማውያን አገር የተቀመጠበት የዘመን ቁጥር አንድ ዓመት ከአራት ወር ነበር።
8ዳዊትና ሰዎቹም ወጥተው በጌሹራውያንና በጌርዛውያን በአማሌቃውያንም ላይ ዘመቱ፥ እነዚህም እስከ ሱር እስከ ግብጽ ምድር ድረስ ባለው አገር ድሮውኑ ተቀምጠው ነበር። 9ዳዊትም ምድሪቱን መታ፥ ወንድ ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም፥ በጎችንና ላሞችን አህያዎችንና ግመሎችን ልብስንም ማረከ፥ ተመልሶም ወደ አንኩስ መጣ። 10አንኩስም፦ ዛሬ በማን ላይ ዘመታችሁ? አለ፥ ዳዊትም፦ በይሁዳ ደቡብ፥ በይረሕምኤላውያንም ደቡብ፥ በቄናውያንም ደቡብ ላይ ዘመትን አለ። 11ዳዊት እንዲህ አደረገ በፍልስጥኤማውያንም አገር በሚቀመጥበት ዘመን ሁሉ ልማዱ ይህ ነበረ ብለው እንዳይናገሩብን ብሎ ዳዊት ወደ ጌት ያመጣቸው ዘንድ ወንድም ሆነ ሴትም ሆነ ማንንም በሕይወት አልተወም። 12አንኩስም፦ በሕዝቡ በእስራኤል ዘንድ እጅግ የተጠላ ሆኖአል፥ ሰለዚህም ለዘላለም ባሪያ ይሆነኛል ብሎ ዳዊትን አመነው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 27: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ