አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16
16
1እግዚአብሔርም ሳሙኤልን፦ በእስራኤል ላይ እንዳይነግሥ ለናቅሁት ለሳኦል የምታለቅስለት እስከ መቼ ነው? በቀንድህ ዘይቱን ሞልተህ ሂድ፥ በልጆቹ መካከል ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ አለው። 2ሳሙኤልም፦ እንዴት እሄዳለሁ? ሳኦል ቢሰማ ይገድለኛል አለ። እግዚአብሔርም፦ አንዲት ጊደር ይዘህ ሂድና፦ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ በል። 3እሴይንም መሥዋዕቱ ጥራው፥ የምታደርገውንም አስታውቅሃለሁ፥ የምነግርህንም ቅባልኝ አለው። 4ሳሙኤልም እግዚአብሔር የተናገረውን አደረገ፥ ወደ ቤተ ልሔምም መጣ። የአገሩም ሽማግሌዎች እየተንቀጠቀጡ ሊገናኙት መጡና፦ የመጣኸው ለደኅንነት ነውን? አሉት። 5እርሱም፦ ለደኅነት ነው፥ ለእግዚአብሔር እሠዋ ዘንድ መጣሁ፥ ቅዱሳን ሁኑ፥ ከእኔም ጋር ወደ መሥዋዕቱ ኑ አለ። እሴይንና ልጆቹንም ቀደሳቸው፥ ወደ መሥዋዕቱም ጠራቸው።
6እንዲህም ሆነ፥ በመጡ ጊዜ ወደ ኤልያብ ተመልክቶ፦ በእውነት እግዚአብሔር የሚቀባው በፊቱ ነው አለ። 7እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፦ ፊቱን የቁመቱንም ዘለግታ አትይ፥ ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና ናቅሁት፥ ሰው ፊትን ያያል፥ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል አለው። 8እሴይም አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት አሳለፈው፥ እርሱም፦ ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። 9እሴይም ሣማን አሳለፈው፥ እርሱም፦ ይህን ደግሞ እግዚአብሔር አልመረጠውም አለ። 10እሴይም ከልጆቹ ሰባቱን በሳሙኤል ፊት አሳለፋቸው። ሳሙኤልም እሴይን፦ እግዚአብሔር እነዚህን አልመረጠም አለው። 11ሳሙኤልም እሴይን፦ የቀረ ሌላ ልጅ አለህን? አለው። እርሱም፦ ታናሹ ገና ቀርቶአል፥ እነሆም፥ በጎችን ይጠብቃል አለ። ሳሙኤልም እሴይን፦ እርሱ እስኪመጣ ድረስ አንረፍቅምና ልከህ አስመጣው አለው። 12ልኮም አስመጣው፥ እርሱም ቀይ፥ ዓይኑም የተዋበ፥ መልኩም ያማረ ነበረ። እግዚአብሔርም፦ ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው አለ። 13ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ መካከል ቀባው። የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያ ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ በኃይል መጣ። ሳሙኤልም ተነሥቶ ወደ አርማቴም ሄደ።
14የእግዚአብሔርም መንፈስ ከሳኦል ራቀ፥ ክፉም መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ አሠቃየው። 15የሳኦልም ባሪያዎች፦ እነሆ ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያሠቃይሃል፥ 16በገና መልካም አድርጎ የሚመታ ሰው ይሹ ዘንድ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን ባሪያዎቹን ይዘዝ፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ክፉ መንፈስ በሆነብህ ጊዜ በእጅ ሲመታ አንተ ደኅና ትሆናለህ አሉት። 17ሳኦልም ባሪያዎቹን፦ መልካም አድርጎ በገና መምታት የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ አላቸው። 18ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፦ እነሆ፥ መልካም አድርጎ በገና የሚመታ የቤተ ልሔማዊውን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፥ እርሱም ጽኑዕ ኃይል ነው፥ በነገርም ብልህ፥ መልኩም ያማረ ነው፥ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው አለ። 19ሳኦልም ወደ እሴይ መልክተኞች ልኮ፦ ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ አለ። 20እሴይም እንጀራና የወይን ጠጅ አቁማዳ የተጫነ አህያ የፍየልም ጠቦት ወስዶ በልጁ በዳዊት እጅ ወደ ሳኦል ላከ። 21ዳዊትም ወደ ሳኦል መጣ፥ በፊቱም ቆመ፥ እጅግም ወደደው፥ ለእርሱም ጋሻ ጃግሬው ሆነ። 22ሳኦልም ወደ እሴይ፦ በዓይኔ ሞገስ አግኝቶአልና ዳዊት በፊቴ፥ እባክህ፥ ይቁም ብሎ ላከ። 23እንዲህም ሆነ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክፉ መንፈስ በሳኦል ላይ በሆነ ጊዜ ዳዊት በገና ይዞ በእጁ ይመታ ነበር፥ ሳኦልም ደስ ያሰኘው ያሳርፈውም ነበር፥ ክፉ መንፈስም ከእርሱ ይርቅ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 16: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ