አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12
12
1ሳሙኤልም እስራኤልን ሁሉ አለ፦ የነገራችሁኝን ሁሉ ሰምቼ አንግሼላችኋለሁ። 2አሁንም፥ እነሆ፥ ንጉሡ በፊታችሁ ይሄዳል እኔም አርጅቻለሁ ሸምግያለሁም፥ እነሆም፥ ልጆቼ ከእናንተ ጋር ናቸው፥ እኔም ከሕፃንነቴ ጀምሬ እስከ ዛሬ ድረስ በፊታችሁ ሄድሁ። 3እነሆኝ፥ በእግዚአሔርና እርሱ በቀባው ፊት መስክሩብኝ፥ የማንን በሬ ወሰድሁ? የማንንስ አህያ ወሰድሁ? ማንንስ ሸነገልሁ? በማንስ ላይ ግፍ አደረግሁ? ዓይኖቼንስ ለማሳወር ከማን ጋር እጅ ጉቦ ተቀበልሁ? እኔም እመልስላችኋለሁ። 4እነርሱም፦ አልሸነገልኸንም፥ ግፍም አላደረግህብንም፥ ከሰውም እጅ ምንም አልወሰድህም አሉ። 5እርሱም፦ በእጄ ምንም እንዳላገኛችሁ እግዚአብሔርና እርሱ የቀባው ዛሬ በእናንተ ላይ ምስክሮች ናቸው አላቸው፥ እነርሱም፦ ምስክር ነው አሉ።
6ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ፦ ሙሴንና አሮንን ያላቀ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ ምድር ያወጣ እግዚአብሔር ነው። 7አሁንም እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ ስላደረገው ጽድቅ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እምዋገታችሁ ዘንድ በዚህ ቁሙ። 8ያዕቆብና ልጆቹ ወደ ግብጽ በገቡ ጊዜ ግብጻውያን አስጨነቁአቸው፥ አባቶቻችሁም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ላከ፥ አባቶቻችሁንም ከግብጽ አውጥተው በዚህ ቦታ አኖሩአቸው። 9አምላካቸውንም እግዚአብሔርን ረሱ፥ ለአሶር ሠራዊትም አለቃ ለሲሣራ እጅ፥ ለፍልስጥኤማውያንም እጅ፥ ለሞዓብም ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ከእነርሱም ጋር ተዋጉ። 10እነርሱም፦ እግዚአብሔርን ትተን በአሊምንና አስታሮትን በማምለካችን በድለናል፥ አሁንም ከጠላቶቻችን እጅ አድነን፥ እናመልክህማለን ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 11እግዚአብሔርም ይሩበአልን፥ ባርቅንም፥ ዮፍታሔንም፥ ሳሙኤልንም ላከ፥ በዙሪያችሁም ካሉት ከጠላቶቻችሁ እጅ አዳናችሁ፥ ተዘልላችሁም ተቀመጣችሁ። 12የአሞንም ልጆች ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ሳለ፦ እንዲህ አይሁን፥ ነገር ግን ንጉሥ ይንገሥልን አላችሁኝ። 13አሁንም የመረጣችሁትንና የፈለጋችሁትን ንጉሥ እዩ፥ እነሆም፥ እግዚአብሔር ንጉሥ አደረገላችሁ። 14እግዚአብሔርን ብትፈሩ ብታመልኩትም፥ ቃሉንም ብትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ባታምፁ፥ እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ብትከተሉ፥ መልካም ይሆንላችኋል። 15ነገር ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ በእግዚአብሔርም ትእዛዝ ላይ ብታምፁ፥ በእናንተና በንጉሣችሁ ላይ የእግዚአብሔር እጅ ትሆናለች። 16አሁንም ቁሙ፥ እግዚአብሔርም በዓይናችሁ ፊት ወደሚያደርገው ወደዚህ ታላቅ ነገር ተመልከቱ። 17የስንዴ መከር ዛሬ አይደለምን? ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፥ እርሱም ነጎድጓድና ዝናብ ይልካል፥ እናንተም ንጉሥ በመለመናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ያደረጋችሁት ክፋት ታላቅ እንደ ሆነ ታውቃላችሁ ታያላችሁም። 18ሳሙኤልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፥ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን ነጎድጓድና ዝናብ ላከ፥ ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩአቸው።
19ሕዝቡም ሁሉ ሳሙኤልን፦ ንጉሥ በመለመናችን በኃጢአታችን ሁሉ ላይ ይህን ክፋት ጨምረናልና እንዳንሞት ስለ ባሪያዎችህ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት። 20ሳሙኤልም ሕዝቡን አለ፦ አትፍሩ፥ በእውነት ይህን ክፋት ሁሉ አደረጋችሁ፥ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችሁ አምልኩት እንጂ እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ አትበሉ። 21ምናምንቴ ነውና የማይረባንና የማያድን ከንቱን ነገር ለመከተል ፈቀቅ አትበሉ። 22እግዚአብሔር ለእርሱ ሕዝብ ያደርጋችሁ ዘንድ ወድዶአልና እግዚአብሔር ስለ ታላቅ ስሙ ሕዝቡን አይተውም። 23ደግሞ መልካሙንና ቅኑን መንገድ አስተምራችኋለሁ እንጂ ስለ እናንተ መጸለይን በመተው እግዚአብሔርን እበድል ዘንድ ይህ ከእኔ ይራቅ። 24ብቻ እግዚአብሔርን ፍሩ፥ ያደረገላችሁንም ታላቅ ነገር አይታችኋልና በፍጹም ልባችሁ በእውነት አምልኩት። 25ነገር ግን ክፉ ብትሠሩ እናንተም ንጉሣችሁም ትጠፋላችሁ።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ