አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 7
7
ሰሎሞን ቤተ መንግሥቱን መሥራቱ
1ሰሎሞንም የራሱን ቤት በዐሥራ ሦስት ዓመት ሠራ፤ የቤቱንም ሥራ ሁሉ ጨረሰ። 2የሊባኖስ ዱር ቤት የሚባል ቤትን ሠራ፤ ርዝመቱንም መቶ ክንድ፥ ስፋቱንም አምሳ ክንድ፥ ቁመቱንም ሠላሳ ክንድ አደረገ፤ የዝግባም እንጨት በሦስት ተራ በተሠሩ አዕማድ ላይ ቆሞ ነበር፤ በአዕማዱም ላይ የዝግባ እንጨት አግዳሚ ሰረገሎች ነበሩ። 3በአዕማዱም ላይ በነበሩ አግዳሚዎች ቤቱ በዝግባ ሳንቃ ተሸፍኖ ነበር፤ አዕማዱም በአንዱ ተራ ዐሥራ አምስት፥ በአንዱ ተራ ዐሥራ አምስት እየሆኑ አርባ አምስት ነበሩ። 4መስኮቶቹም በሦስት ተራ ነበሩ፤ መስኮቶቹም ፊት ለፊት ይተያዩ ነበሩ። 5ደጆቹና መስኮቶቹም ሁሉ አራት ማዕዘን ነበሩ፤ መስኮቶቹም በሦስት ተራ ሆነው ፊት ለፊት ይተያዩ ነበር። 6አዕማዱም ያሉበትን ቤት ሠራ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ስፋቱም ሠላሳ ክንድ ነበረ፤ በእርሱም ፊት ደግሞ አዕማድና መድረክ ያሉበት ወለል ነበረ። 7ደግሞም የሚፈርድበት ዙፋን ያለበትን የፍርድ ቤት አደረገ። ከወለሉም አንሥቶ እስከ ጣራው ድረስ በዝግባ እንጨት ተሸፍኖ ነበር። 8ከፍርድ ሰቀላ ወደ ውስጥ፥ በሌላውም አደባባይ ውስጥ የነበረውን መኖሪያ ቤት እንዲሁ ሠራ። እንደዚሁም ያለ ቤት ሰሎሞን ላገባት ለፈርዖን ልጅ ቤት ሠራ።
9እነዚህም ሁሉ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጉልላቱ ድረስ በጥሩ በተጠረበና በውስጥና በውጭ በልክ በተከረከመ ድንጋይ ተሠርተው ነበር፤ በውጭውም እስከ ታላቁ አደባባይ ድረስ እንዲሁ ነበረ። 10መሠረቱም ዐሥር ወይም ስምንት ክንድ በሆነ በጥሩና በታላቅ ድንጋይ ተሠርቶ ነበር። 11በላዩም ልክ ሆኖ የተከረከመ ጥሩ ድንጋይና የዝግባ ሳንቃ ነበረ። 12በታላቁም አደባባይ ዙሪያ የነበረው ቅጥር እንደ እግዚአብሔር ቤት እንደ ውስጠኛው አደባባይ ቅጥርና እንደ ቤቱ ወለል ሦስቱ ተራ በተጠረበ ድንጋይ አንዱም ተራ በዝግባ ሳንቃ ተሠርቶ ነበር።
ከነሐስ የተሠሩ የቤተ መቅደስ ዕቃዎች
(2ዜ.መ. 3፥15-17፤ 4፥2-5)
13ንጉሡም ሰሎሞን ልኮ ኪራምን ከጢሮስ አስመጣ። 14እርሱም ከንፍታሌም ወገን የነበረች የባል አልባ ሴት ልጅ ነበረ፤ አባቱም የጢሮስ ሰው ናስ ሠራተኛ ነበረ፤ የናስንም ሥራ ሁሉ ይሠራ ዘንድ በጥበብ በማስተዋል በብልሃትም ተሞልቶ ነበር። ወደ ንጉሡም ወደ ሰሎሞን መጥቶ ሥራውን ሁሉ ሠራ። 15ሁለቱን የናስ አዕማድ አደረገ፤ የአንዱም ዐምድ ቁመት ዐሥራ ስምንት ክንድ ነበረ፤ የዙሪያውም መጠን ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፤ የዐምዱም ውፍረት አንድ ጋት ነበረ፤ ውስጠ ክፍትም ነበረ። ሁለተኛውም ዐምድ እንዲሁ ነበረ። 16በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ እንዲቀመጡ ከፈሰሰ ናስ ሁለት ጕልላት ሠራ፤ የአንዱም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ፥ የሁለተኛውም ጕልላት ቁመት አምስት ክንድ ነበረ። 17በአዕማዱም ራስ ላይ የነበሩትን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ሁለት እንደ መርበብ ሥራ አደረገ፤ አንዱም መርበብ ለአንዱ ጕልላት ሁለተኛውም መርበብ ለሁለተኛው ጕልላት ነበረ። 18ሮማኖችንም ሠራ፤ በአንድ ጕልላት ዙሪያ በተራ ሁለት መቶ ሮማኖች ነበሩ፤ በአንድም መርበብ ላይ ሁለት ተራ ነበረ፤ እንዲሁም ለሁለተኛው ጕልላት አደረገ። 19በወለሉም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ አራት ክንድ አድርጎ ቀረጸ። 20በሁለቱም አዕማድ በነበሩት ጕልላቶች ላይ በመርበቡ ሥራ አጠገብ ሮማኖቹን አደረገ። 21አዕማዱንም በመቅደሱ ወለል አጠገብ አቆማቸው፤ የቀኙንም ዐምድ አቁሞ ያቁም ብሎ ጠራው፤ የግራውንም ዐምድ አቁሞ በለዝ ብሎ ጠራው። 22በአዕማዱም ራስ ላይ የሱፍ አበባ የሚመስል ሥራ ነበር፤ እንዲሁም የአዕማዱ ሥራ ተጨረሰ።
23ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ። 24ከከንፈሩም በታች ለአንድ ክንድ ዐሥር ለአንድ ክንድም ዐሥር ጉብጉቦች አዞረበት፤ እርሱም በቀለጠ ጊዜ ጉብጉቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። 25ኵሬውም በዐሥራ ሁለት በሬዎች ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር። ኵሬውም በላያቸው ነበረ፤ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። 26ውፍረቱም አንድ ጋት ነበረ፤ ከንፈሩም እንደ ጽዋ ከንፈር ተሠርቶ ነበር፤ እንደ ሱፍ አበባዎች ሆኖ ተከርክሞ ነበር። ሁለት ሺህም የባዶስ መስፈሪያ ይይዝ ነበር።
27ዐሥርም የናስ መቀመጫዎች ሠራ፤ የአንዱም መቀመጫ ርዝመት አራት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ ነበረ። 28የመቀመጫውም ሥራ እንዲህ ነበረ፤ በክፈፎችም መካከል ያለው ሰንበር ይመስል ነበር። 29በክፈፎቹም መካከል በነበሩ ሰንበሮች ላይ አንበሳዎችና በሬዎች ኪሩቤልም ነበሩ፤ እንዲሁም በክፈፎቹ ላይ ነበረ፤ ከአንበሳዎቹና ከበሬዎቹ በታች ሻኵራ የሚመስል ተንጠልጥሎ ነበር። 30በየመቀመጫዎቹም ሁሉ አራት የናስ መኰራኵሮች ነበሩባቸ፤ መንኰራኵሮቹም የሚዞሩበትን የናስ ወስከምት ሠራ፤ ከመታጠቢያውም ሰን በታች በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት በምስል የፈሰሱ እግሮች ነበሩ። 31በክፈፉም ውስጥ የነበረ አንገት አንድ ክንድ ነበረ፤ አንገቱም ድቡልቡል ነበረ፤ ቁመቱም ክንድ ተኩል ነበረ። በአንገቱም ላይ ቅርጽ ነበረበት፤ ክፈፉ ግን አራት ማዕዘን ነበረ እንጂ ድቡልቡል አልነበረም። 32አራቱም መንኰራኵሮች ከሰንበሮቹ በታች ነበሩ፤ የመንኰራኵሮቹም ወስከምት በመቀመጫው ውስጥ ነበረ፤ የመኰራኵሩም ቁመት ክንድ ተኩል ነበረ። 33የመንኰራኵሮቹም ሥራ እንደ ሠረገላ መንኰራኵር ነበረ፤ ወስከምቶቹና የመንኰራኵሮቹ ክፈፍ ቅትርቶቹም ወስከምቱም የሚገባበት ቧምቧ ሁሉ በምስል የፈሰሰ ነበረ። 34በእያንዳንዱም መቀመጫ በአራቱ ማዕዘን በኩል አራት ደገፋዎች ነበሩ፤ ደገፋዎቹም ከመቀመጫው ጋር ተገጥመው ነበር። 35በመቀመጫውም ላይ ስንዝር የሚሆን ድቡልቡል ነገር ነበረ፤ በመቀመጫውም ላይ የነበሩ መያዣዎችና ሰንበሮች ከእርሱ ጋር ይጋጠሙ ነበር። 36በመያዣውና በሰንበሮቹ ላይ ኪሩቤልንና አንበሳዎችን የዘንባባውንም ዛፍ እንደ መጠናችው ቀረጸ፤ በዙሪያውም ሻኵራ አደረገ። 37እንዲሁ ዐሥሩን መቀመጫዎች ሠራ፤ ሁሉም በምስልና በመጠን በንድፍም ትክክሎች ነበሩ።
38ዐሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በዐሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር። 39አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው።
የቤተ መቅደሱ ዕቃዎች ዝርዝር
(2ዜ.መ. 4፥11—5፥1)
40ኪራምም ምንቸቶችንና መጫሪያዎችን ድስቶችንም ሠራ፤ ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። 41ሁለቱም አዕማድ፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ኩብ የሚመስሉትን ጕልላቶች፥ በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች፥ 42በአዕማዱም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ለእያንዳንዱ መርበብ በሁለት በሁለት ተራ አድርጎ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ። 43ዐሥሩንም መቀመጫዎች፥ በመቀመጫዎችም ላይ የሚቀመጡትን ዐሥሩን መታጠቢያ ሰን፥ 44አንዱንም ኵሬ፥ ከኵሬውም በታች የሚሆኑትን ዐሥራ ሁለቱን በሬዎች፥ 45ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም አደረገ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራው ይህ ዕቃ ሁሉ የጋለ ናስ ነበረ። 46በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጸርታን መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው። 47ሰሎሞንም ዕቃውን ሁሉ ሳያስመዝን አኖረ፤ የናሱም ሚዛን ከብዛቱ የተነሣ አይቆጠርም ነበር።
48ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ አሠራ፤ የወርቁን መሠዊያ፥ የገጹም ኅብስት የነበረበትን የወርቅ ገበታ፥ 49በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት አምስቱ በቀኝ አምስቱም በግራ የሚቀመጡትን ከጥሩ ወርቅ የተሠሩትንም መቅረዞች፥ የወርቁንም አበባዎችና ቀንዲሎች መኮስተሪያዎችም፥ 50ከጥሩ ወርቅም የተሠሩትን ጽዋዎችና ጕጠቶች፥ ድስቶቹንና ጭልፋዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም፥ ለውስጠኛውም ቤት ለቅድስተ ቅዱሳን ደጆች ለቤተ መቅደሱም ደጆች የሚሆኑትን የወርቅ ማጠፊያዎች አሠራ።
51እንዲሁ ንጉሡ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሠራው ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ ብርና ወርቅ፥ ዕቃም፥ ሰሎሞን አገባ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ውስጥ በነበሩ ግምጃ ቤቶች አኖረው።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ