የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 27

27
የሠራዊቱ ዋና ዋና ክፍሎች
1የእስራኤልም ልጆች የአባቶች ቤቶች አለቆችና የሺህ አለቆች የመቶ አለቆችም በክፍሎች ነገር ሁሉ ንጉሡን ያገለገሉትም ሹማምት እንደ ቍጥራቸው እነዚህ ነበሩ። እነዚህም ክፍሎች እያንዳንዳቸው ሃያ አራት ሺህ ሆነው በዓመት ወራት ሁሉ በየወሩ ይገቡና ይወጡ ነበር። 2ለመጀመሪያው ወር በአንደኛው ክፍል ላይ የዘብድኤል ልጅ ያሾብዓም ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 3እርሱ ከፋሬስ ልጆች ነበረ፤ ለመጀመሪያ ወር በጭፍራ አለቆች ሁሉ ላይ ተሹሞ ነበር። 4በሁለተኛውም ወር ክፍል ላይ አሆሃዊው ዱዲ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 5ለሦስተኛው ወር ሦስተኛው የጭፍራ አለቃ የካህኑ የዮዳሄ ልጅ በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 6ይህ በናያስ በሠላሳው መካከል ኀያል ሆኖ በሠላሳው ላይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ልጁ ዓሚዛባድ ነበረ። 7ለአራተኛው ወር አራተኛው አለቃ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ ከእርሱም በኋላ ልጁ ዝባድያ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 8ለአምስተኛው ወር አምስተኛው አለቃ ይዝራዊው ሸምሁት ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 9ለስድስተኛው ወር ስድስተኛው አለቃ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 10ለሰባተኛው ወር ሰባተኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የሆነ ፍሎናዊው ሴሌስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 11ለስምንተኛው ወር ስምንተኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ኩሳታዊው ሲቦካይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 12ለዘጠነኛው ወር የዘጠነኛው አለቃ ከብንያማውያን የነበረው ዓናቶናዊው አቢዔዘር ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 13ለዐሥረኛው ወር ዐሥረኛው አለቃ ከዛራውያን የነበረው ነጦፋዊው ኖኤሬ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 14ለዐሥራ አንደኛው ወር ዐሥራ አንደኛው አለቃ ከኤፍሬም ልጆች የነበረው ጲርዓቶናዊው በናያስ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ። 15ለዐሥራ ሁለተኛው ወር ዐሥራ ሁለተኛው አለቃ ከጎቶንያል ወገን የነበረው ነጦፋዊው ሔልዳይ ነበረ፤ በእርሱም ክፍል ሃያ አራት ሺህ ጭፍራ ነበረ።
የየነገዱ መሪዎች
16በእስራኤልም ነገዶች ላይ እነዚህ ነበሩ፤ በሮቤላውያን ላይ የዝክሪ ልጅ አልዓዛር አለቃ ነበረ፤ በስማዖናውያን ላይ የመዓካ ልጅ ሰፋጥያስ፤ 17በሌዊ ላይ የቀሙኤል ልጅ ሐሸብያ፤ በአሮን ላይ ሳዶቅ፤ 18በይሁዳ ላይ ከዳዊት ወንድሞች ኢሊሁ፤ በይሳኮር ላይ የሚካኤል ልጅ ዖምሪ፤ 19በዛብሎን ላይ የአብድዩ ልጅ ይሽማያ፤ በንፍታሌም ላይ የዓዝሪኤል ልጅ ኢያሪሙት፤ 20በኤፍሬም ልጆች ላይ የዓዛዝያ ልጅ ሆሴዕ፤ በምናሴ ነገድ እኵሌታ ላይ የፈዳያ ልጅ ኢዩኤል፤ 21በገለአድ ባለው በምናሴነገድ እኵሌታ ላይ የዘካርያስ ልጅ አዶ፤ በብንያም ላይ የአብኔር ልጅ የዕሢኤል፤ 22በዳን ላይ የይሮሐም ልጅ ዓዛርኤል፤ እነዚህ የእስራኤል ነገዶች አለቆች ነበሩ። 23እግዚአብሔር ግን እስራኤልን እንደ ሰማይ ከዋክብት ያበዛ ዘንድ ተናግሮ ነበርና ዳዊት ከሃያ ዓመት በታች የነበሩትን አልቈጠረም። 24የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ መቍጠር ጀመረ፥ ነገር ግን አልፈጸመም፤ ስለዚህም በእስራኤል ላይ ቍጣ ሆነ፥ ቍጥራቸውም በንጉሡ በዳዊት መዝገብ አልተጻፈም።
የቤተ መንግሥት ንብረት አስተዳዳሪዎች
25በንጉሡም ቤተ መዛግብት ላይ የዓዲኤል ልጅ ዓዛሞት ሹም ነበረ፤ በሜዳውም በከተሞችም በመንደሮችም በግንቦችም ቤተ መዛግብት ላይ የዖዝያ ልጅ ዮናታን ሹም ነበረ፤ 26መሬቱን በሚያበጃጁትና እርሻውን በሚያርሱት ላይ የክሉብ ልጅ ዔዝሪ ሹም ነበረ፤ 27በወይንም ቦታዎች ላይ ራማታዊው ሰሜኢ ሹም ነበረ፤ ለወይንም ጠጅ ዕቃ ቤት በሚሆነው በወይኑ ሰብል ላይ ሸፋማዊው ዘቢድ ሹም ነበረ። 28በቈላውም ውስጥ ባሉት በወይራውና በሾላው ዛፎች ላይ ጌድራዊው በአልሐናን ሹም ነበረ፤ በዘይቱም ቤቶች ላይ ኢዮአስ ሹም ነበረ፤ 29በሳሮንም በሚሰማሩ ከብቶች ላይ ሳሮናዊው ሰጥራይ ሹም ነበረ፤ በሸለቆቹም ውስጥ በነበሩት ከብቶች ላይ የዓድላይ ልጅ ሻፋጥ ሹም ነበረ፤ 30በግመሎችም ላይ እስማኤላዊው ኡቢያስ ሹም ነበረ፤ በአህዮቹም ላይ ሜሮኖታዊው ዬሕድያ ሹም ነበረ፤ 31በመንጎቹም ላይ አጋራዊው ያዚዝ ሹም ነበረ። እነዚህ ሁሉ በንጉሡ በዳዊት ሀብት ላይ ሹሞች ነበሩ።
የዳዊት የግል አማካሪዎች
32አስተዋይና ጸሐፊ የነበረው የዳዊት አጎት ዮናታን አማካሪ ነበረ፤ የሐክሞኒም ልጅ ይሒኤል ከንጉሡ ልጆች ጋር ነበረ፤ 33አኪጦፌልም የንጉሡ አማካሪ ነበረ፤ አርካዊውም ኩሲ የንጉሡ ወዳጅ ነበረ፤ 34ከአኪጦፌልም ቀጥሎ የበናያስ ልጅ ዮዳሄና አብያታር ነበሩ፤ ኢዮአብያም የንጉሡ ሠራዊት አለቃ ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ