አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12
12
ከብንያም ነገድ ዳዊትን የተከተሉ ተዋጊዎች
1በጺቅላግም ከቂስ ልጅ ከሳኦል በተሸሸገ ጊዜ ወደ ዳዊት የመጡ እነዚህ ናቸው፤ በሰልፍም ባገዙት ኀያላን መካከል ነበሩ። 2ቀስተኞችም ነበሩ፤ በቀኝና በግራም እጃቸው ድንጋይ ሊወነጭፉ ፍላጻም ሊወረውሩ ይችሉ ነበር፤ ከብንያም ወገን የሳኦል ወንድሞች ነበሩ። 3አለቃቸው አሒዔዝር ነበረ፤ ከእርሱም በኋላ ኢዮአስ፥ የጊብዓዊው የሸማዓ ልጆች ይዝኤል፥ ፋሌጥ፥ የዓዝሞት ልጆች በራኪያ፥ ዓናቶታዊው ኢዩ፥ 4ገባዖናዊው ሰማያስ፥ እርሱ በሠላሳው መካከልና በሠላሳው ላይ ኀያል ሰው ነበረ፤ ኤርምያስ፥ የሕዚኤል፥ ዮሐናን፥ ገድሮታዊ ዮዛባት፥ 5ኤሉዛይ፥ ኢያሪሙት፥ በዓልያ፥ ሰማራያ፥ ሐሩፋዊው ሰፋጥያስ፥ 6ቆሬያውያን ሕልቃና፥ ይሺያ፥ ዓዘርኤል፥ ዮዛር፥ ያሾብዓም፤ 7የጌዶር ሰው የይሮሐም ልጆች ዮዔላና ዝባድያ።
ከጋድ ነገድ ዳዊትን የተከተሉ ተዋጊዎች
8ዳዊትም በምድረ በዳ ውስጥ ባለችው በአምባይቱ ሳለ ከጋድ ወገን የሆኑ እነዚህ ጋሻና ጦር የሚይዙ፥ ጽኑዓን፥ ኃያላን፥ ሰልፈኞች ወደ እርሱ ተጠጉ፤ ፊታቸውም እንደ አንበሳ ፊት ነበረ፤ በተራራም ላይ እንደሚዘልል ሚዳቋ ፈጣኖች ነበሩ። 9አለቃው ዔጼር፥ ሁለተኛው አብድዩ፥ ሦስተኛው ኤልያብ፥ 10አራተኛው መስመና፥ አምስተኛው ኤርምያስ፥ 11ስድስተኛው ዓታይ፥ ሰባተኛው ኤሊኤል፥ 12ስምንተኛው ዮሐናን፥ ዘጠነኛው ኤልዛባድ፥ 13ዐሥረኛው ኤርምያስ፥ ዐሥራ አንደኛው መክበናይ። 14እነዚህ የጋድ ልጆች የጭፍራ አለቆች ነበሩ፤ ከእነርሱም ታናሹ ከመቶ፥ ታላቁ ከሺህ ይመዛዘኑ ነበር። 15በመጀመሪያው ወር ዮርዳኖስ ከዳር እስከ ዳር ሞልቶ በነበረ ጊዜ የተሻገሩት እነዚህ ናቸው፤ በሸለቆውም ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ በኩል የተቀመጡትን ሁሉ አባረሩ።
ከብንያምና ከይሁዳ ነገዶች ዳዊትን የተከተሉ ተዋጊዎች
16ዳዊትም ወደ ነበረባት ወደ አምባይቱ ከብንያምና ከይሁዳ ወገን ሰዎች መጡ። 17ዳዊትም ሊገናኛቸው ወጥቶ “ትረዱኝ ዘንድ በሰላም ወደ እኔ መጥታችሁ እንደ ሆነ ልቤ ከእንናተ ጋር አንድ ይሆናል፤ ለጠላቶቼ አሳልፋችሁ ልትሰጡኝ መጥታችሁ እንደ ሆነ ግን፥ በእጄ አመፅ የለብኝምና የአባቶቻችን አምላክ ይመልከተው፤ ይፍረደውም፤” አላቸው። 18መንፈስም በሠላሳው አለቃ በዓማሣይ ላይ መጣ፤ እርሱም “ዳዊት ሆይ! እኛ የአንተ ነን፤ የእሴይ ልጅ ሆይ! እኛ ከአንተ ጋር ነን፤ አምላክህ ይረዳሃልና ሰላም ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ለሚረዱህም ሰላም ይሁን፤” አለ። ዳዊትም ተቀበላቸው፤ የጭፍራም አለቆች አደረጋቸው።
ከምናሴ ነገድ ዳዊትን የተከተሉ ተዋጊዎች
19ዳዊትም ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሳኦልን ሊወጋ በመጣ ጊዜ ከምናሴ ወገን ሰዎች ወደ ዳዊት ከዱ፤ የፍልስጥኤማውያን አለቆች ግን “በራሳችን ላይ ጕዳት አድርጎ ወደ ጌታው ወደ ሳኦል ይመለሳል፤” ሲሉ ተማክረው ሰድደውታልና እነርሱ አልረዱአቸውም። 20ወደ ጺቅላግም ሲሄድ ከምናሴ ወገን የምናሴ ሻለቆች የነበሩ ዓድና፥ ዮዛባት፥ ይዲኤል፥ ሚካኤል፥ ዮዛባት፥ ኤሊሁ፥ ጺልታይ ወደ እርሱ ከዱ። 21ሁሉም ጽኑዓን፥ ኀያላንና በሠራዊቱ ላይ አለቆች ነበሩና በአደጋ ጣዮቹ ላይ ዳዊትን አገዙት። 22እንደ እግዚአብሔርም ሠራዊት ታላቅ ሠራዊት እስኪሆን ድረስ ዳዊትን ለመርዳት ዕለት ዕለት ይመጡ ነበር።
የዳዊት ሠራዊት ብዛት
23እንደ እግዚአብሔርም ቃል የሳኦልን መንግሥት ወደ እርሱ ይመልሱ ዘንድ በኬብሮን ሳለ ወደ ዳዊት የመጡት የሠራዊቱ አለቆች ቍጥር ይህ ነው። 24ጋሻና ጦር ተሸክመው ለሰልፍ የተዘጋጁ የይሁዳ ልጆች ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 25ለሰልፍ ጽኑዓን፥ ኀያላን ሰዎች የነበሩ የስምዖን ልጆች ሰባት ሺህ አንድ መቶ ነበሩ። 26የሌዊ ልጆች አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 27የአሮንም ቤት አለቃ ዮዳሄ ነበረ፤ ከእርሱም ጋር ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ፤ 28ከእርሱም ጋር ጽኑዕ፥ ኀያል ጐልማሳ ሳዶቅ ነበረ፤ ከአባቱም ቤት ሃያ ሁለት አለቆች ነበሩ። 29የሳኦልም ወንድሞች ከሆኑ ከብንያም ልጆች የሚበልጠው ክፍል እስከዚያ ዘመን ድረስ የሳኦልን ቤት ይከተል ነበርና ከእነርሱ ዘንድ የመጡ ሦስት ሺህ ነበሩ። 30ጽኑዓን፥ ኀያልን የሆኑ በአባቶቻቸውም ቤት የታወቁ የኤፍሬም ልጆች ሃያ ሺህ ስምንት መቶ ነበሩ። 31በየስማቸውም የተጻፉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ የመጡ የምናሴ ነገድ እኵሌታ ዐሥራ ስምንት ሺህ ነበሩ። 32እስራኤልም የሚገባውን ያደርግ ዘንድ ዘመኑን የሚያውቁ ጥበበኞች ሰዎች የይሳኮር ልጆች አለቆች ሁለት መቶ ነበሩ፤ ወንድሞቻቸውም ሁሉ ይታዘዙአቸው ነበር። 33በጭፍራውም ውስጥ የወጡ ለሰልፍም የተዘጋጁ፥ የማያመነቱ፥ መሣሪያም ሁሉ የያዙ የዛብሎን ሰዎች አምሳ ሺህ ነበሩ። 34የንፍታሌምም አለቆች አንድ ሺህ ነበሩ፤ ከእነርሱም ጋር ጋሻና ጦር የሚይዙ ሠላሳ ሰባት ሺህ ነበሩ። 35ለሰልፍም የተዘጋጁ የዳን ሰዎች ሃያ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 36በጭፍራውም ውስጥ የሚወጡ፥ ለሰልፍም የተዘጋጁ የአሴር ሰዎች አርባ ሺህ ነበሩ። 37በዮርዳኖስም ማዶ ካሉ ከሮቤልና ከጋድ ሰዎች ከምናሴም ነገድ እኵሌታ መሣሪያን ሁሉ ይዘው የመጡ መቶ ሃያ ሺህ ነበሩ።
38እነዚህ ሁሉ ዳዊትን በእስራኤል ሁሉ ላይ ያነግሡት ዘንድ አርበኞችና ሰልፈኞች እየሆኑ በፍጹም ልባቸው ወደ ኬብሮን መጡ፤ ደግሞም ከእስራኤል የቀሩት ሁሉ ዳዊትን ያነግሡት ዘንድ አንድ ልብ ነበሩ። 39ወንድሞቻቸውም አዘጋጅተውላቸው ነበርና እየበሉና እየጠጡ በዚያ ከዳዊት ጋር ሦስት ቀን ተቀመጡ። 40ደግሞም በእስራኤል ዘንድ ደስታ ሆኖአልና እስከ ይሳኮርና እስከ ዛብሎን እስከ ንፍታሌምም ድረስ ለእርሱ አቅራቢያ የነበሩ በአህያና በግመል በበቅሎና በበሬ ላይ እንጀራና ዱቄት የበለስ ጥፍጥፍና የዘቢብ ዘለላ የወይንም ጠጅ ዘይትም በሬዎችንና በጎችንም በብዙ አድርገው ያመጡ ነበር።
Currently Selected:
አንደኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 12: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ