ትንቢተ ዘካርያስ 8
8
1የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ ጽዮን ታላቅ ቅንዓት ቀንቻለሁ፥ በታላቅም ቍጣ ስለ እርስዋ ቀንቻለሁ። 3እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ጽዮን ተመልሻለሁ፥ በኢየሩሳሌምም መካከል እኖራለሁ፣ ኢየሩሳሌምም የእውነት ከተማ ትባላለች፣ የሠራዊትም ጌታ የእግዚአብሔር ተራራ የተቀደሰ ተራራ ይባላል። 4የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዳግመኛ ሽማግሌዎችና ባልቴቶች በኢየሩሳሌም አደባባይ ይቀመጣሉ፣ ሰውም ሁሉ ከዕድሜው ብዛት የተነሣ ምርኩዝ በእጁ ይይዛል። 5የከተማይቱም አደባባዮች በእነዚያ በሚጫወቱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ይሞላሉ። 6የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህ ወራት በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ዓይን ዘንድ ድንቅ ቢሆን፥ በውኑ በእኔ ዓይን ዘንድ ደግሞ ድንቅ ይሆናልን? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 7የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ሕዝቤን ከምሥራቅ ምድርና ከምዕራብ ምድር አድነዋለሁ፣ 8አመጣቸዋለሁም፥ በኢየሩሳሌምም ውስጥ ይኖራሉ፣ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል፥ እኔም በእውነትና በጽድቅ አምላክ እሆናቸዋለሁ።
9የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መቅደሱ ይሠራ ዘንድ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቤት ከተመሠረተበት ቀን ጀምሮ ከነቢያት አፍ ይህን ቃል በዚህ ዘመን የሰማችሁ እናንተ ሆይ፥ እጃችሁን አበርቱ። 10ከዚያ ወራት አስቀድሞ ለሰውና ለእንስሳ ዋጋ አልነበረምና፣ እኔም ሰውን ሁሉ በወንድሙ ላይ አስነሥቼ ነበርና ከአስጨናቂው የተነሣ ለሚገባውና ለሚወጣው ሰላም አልነበረም። 11አሁን ግን እንደ ቀደመው ዘመን በዚህ ሕዝብ ቅሬታ ላይ አልሆንም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 12ነገር ግን ሰላምን እዘራለሁ፣ ወይኑ ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም አዝመራዋን ታወጣለች፥ ሰማያትም ጠላቸውን ይሰጣሉ፣ ለዚህም ሕዝብ ቅሬታ ይህን ነገር ሁሉ አወርሳለሁ። 13የይሁዳ ቤትና የእስራኤል ቤት ሆይ፥ በአሕዛብ ዘንድ እርግማን እንደ ነበራችሁ፥ እንዲሁ አድናችኋለሁ፥ በረከትም ትሆናላችሁ፣ አትፍሩ፥ እጃችሁንም አበርቱ።
14የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ አባቶቻችሁ እጅግ ባስቈጡኝ ጊዜ ክፉ ለማድረግ እንዳሰብሁ፥ እንዳልተጸጸትሁም፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ 15እንዲሁ ዳግመኛ ለኢየሩሳሌምና ለይሁዳ ቤት በዚህ ወራት በጎነትን አደርግ ዘንድ አስቤአለሁ፣ አትፍሩ። 16የምትሠሩት ነገር ይህ ነው፣ እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ፣ በበር አደባባያችሁም የእውነትንና የሰላምን ፍርድ ፍረዱ፣ 17ሁላችሁም በባልንጀራችሁ ላይ ክፉን ነገር በልባችሁ አታስቡ፣ የሐሰትንም መሐላ አትውደዱ፣ ይህን ነገር ሁሉ እጠላለሁና፥ ይላል እግዚአብሔር።
18የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 19የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአራተኛው ወር ጾም የአምስተኛውም የሰባተኛውም የአሥረኛውም ወር ጾም ለይሁዳ ቤት ደስታና ተድላ የሐሤትም በዓላት ይሆናል፣ ስለዚህም እውነትንና ሰላምን ውደዱ። 20የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በብዙ ከተሞች የሚቀመጡ አሕዛብ ገና ይመጣሉ፣ 21በአንዲትም ከተማ የሚኖሩ ሰዎች፦ እግዚአብሔርን እንለምን ዘንድ፥ የሠራዊትንም ጌታ እግዚአብሔርን እንፈልግ ዘንድ ኑ እንሂድ፣ እኔም እሄዳለሁ እያሉ ወደ ሌላ ከተማ ይሄዳሉ። 22ብዙ ወገኖችና ኃይለኞች አሕዛብ በኢየሩሳሌም የሠራዊትን ጌታ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርንም ይለምኑ ዘንድ ይመጣሉ። 23የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው፦ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዘካርያስ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ