ወንድሞች ሆይ፥ እኔም በጎ ምግባርን ሁሉ እንደምትፈጽሙ እታመንባችኋለሁ፤ እናንተ ፍጹም ዕውቀትን የተመላችሁ ናችሁ፤ ባልንጀሮቻችሁንም ልታስተምሩአቸው ትችላላችሁ። ከእግዚአብሔር ስለ አገኘሁት ጸጋ ላሳስባችሁ በአንዳንድ ቦታ በድፍረት ጻፍሁላችሁ። በአሕዛብ መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን አገለግል ዘንድ፥ ለእግዚአብሔር ወንጌልም እገዛ ዘንድ፥ በእኔ ትምህርት አሕዛብ በመንፈስ ቅዱስ የተወደደና የተመረጠ መሥዋዕት ይሆኑ ዘንድ። ለእኔም በእግዚአብሔር ዘንድ መመኪያዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አሕዛብም እንዲያምኑ ክርስቶስ በቃልም በሥራም ያደረገልኝን እናገር ዘንድ እደፍራለሁ። በኀይልና በተአምራት፥ በመንፈስ ቅዱስ ኀይልና ድንቅ ሥራን በመሥራትም፥ ከኢየሩሳሌም አውራጃዎች ጀምሬ እስከ እልዋሪቆን ድረስ እንደ አስተማርሁ፥ የክርስቶስንም ወንጌል ፈጽሞ እንደ ሰበክሁ እናገር ዘንድ እደፍራለሁ። ወንጌልን ለማስተማር ተጋሁ፤ ነገር ግን በሌላ መሠረት ላይ እንዳላንጽ የክርስቶስ ስም ወደ ተጠራበት አልሄድሁም። “ወሬው ያልደረሳቸው ያውቁታል፤ ያልሰሙትም ያስተውሉታል” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ ነው። ዘወትር ወደ እናንተ ልመጣ እወድድ ነበር፤ ነገር ግን ተሳነኝ። አሁን ግን በዚህ ሀገር ሥራዬን ስለ ጨረስሁ፥ ከብዙ ጊዜም ጀምሮ ወደ እናንተ ልመጣ እተጋ ስለ ነበር፤ ወደ አስባንያ ስሄድ እግረ መንገዴን ላያችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ቀደም ብዬ ከእናንተ ጋር ደስ ካለኝ በኋላም ከእናንተ ወደዚያ እሄዳለሁ። አሁን ግን ቅዱሳንን ለመርዳት ወደ ኢየሩሳሌም እሄዳለሁ። መቄዶንያና አካይያ በኢየሩሳሌም ቅዱሳን መካከል ላሉ ድሆች አስተዋጽፅኦ ለማድረግ ተባብረዋልና። የሚገባቸውም ሰለሆነ በመንፈሳዊ ሥራ አሕዛብን ከተባበሩአቸው ለሰውነታቸው በሚያስፈልጋቸው ሊረዱአቸው ይገባል። እንግዲህ ይህን ፍሬ ጨርሼና አትሜ በእናንተ በኩል ወደ አስባንያ እሄዳለሁ። ነገር ግን በመጨረሻ ጊዜ በክርስቶስ ወንጌል በረከት ፍጹምነት እንደምትመጣ አምናለሁ። ወንድሞች፥ በጸሎታችሁ ስለ እኔ ወደ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ትተጉ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ፍቅር እማልዳችኋለሁ። ይኸውም በኢየሩሳሌም ያሉ ቅዱሳንን በአገልግሎቴ ደስ አሰናቸው ዘንድ በይሁዳ ሀገር ካሉ ዐላውያን እንዲያድነኝ ነው። እግዚአብሔርም ቢፈቅድ በደስታ ወደ እናንተ መጥቼ ከእናንተ ጋር ዐርፍ ዘንድ ነው። የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን።
ወደ ሮሜ ሰዎች 15 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ሮሜ ሰዎች 15
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ሮሜ ሰዎች 15:14-33
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች