ወደ ሮሜ ሰዎች 10
10
ስለ ጳውሎስ ፈቃድ
1ወንድሞች፥ የእኔስ የልቤ ምኞት፥ ወደ እግዚአብሔር የማቀርበው ጸሎትም እስራኤል እንዲድኑ ነው። 2ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ ምስክራቸው እኔ ነኝና፤ ነገር ግን ዐውቀው አይደለም። 3የእግዚአብሔርን ጽድቅ አያውቁአትምና በራሳቸውም ጽድቅ ጸንተው ሊኖሩ ወደዱ፤ ለእግዚአብሔር ጽድቅ ግን መገዛት ተሳናቸው። 4የኦሪት ጽድቅ ፍጻሜስ ለሚያምኑበት ሁሉ በክርስቶስ ማመን ነው። 5#ዘሌ. 18፥5። ሙሴም “የኦሪትን ጽድቅ መሥራትን የፈጸመ ሁሉ በእርሱ ይጸድቅበታል” አለ። 6የእምነት ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፥ “በልብህ ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?” አትበል፤ ከሰማይ የወረደው ክርስቶስ ነው።#ግሪኩ “ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው” ይላል። 7“ወደ ጥልቁም ማን ይወርዳል?” አትበል፤ ከሙታን ተለይቶ የተነሣው ክርስቶስ ነው።#ግሪኩ “ይህ ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው” ይላል። 8#ዘዳ. 30፥12-14። መጽሐፍ እንዲሁ፥ “ቃል ለልብህም ለአፍህም ቀርቦልሃል ይል የለምን?” ይህም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። 9ኢየሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን ለይቶ እንደ አስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ። 10በልቡ የሚያምን ይጸድቃልና፤ በአፉም የሚመሰክር ይድናልና። 11#ኢሳ. 28፥16። መጽሐፍ፥ “የሚያምንበት ሁሉ አያፍርም” ብሎአል። 12አይሁዳዊንና አረማዊን አልለየም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ እግዚአብሔር ባለጸጋ ስለሆነ ለለመነው ሁሉ ይበቃልና። 13#ኢዩ. 2፥32። “የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” 14ነገር ግን ያላመኑበትን እንዴት ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? 15#ኢሳ. 52፥7። “መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው?” ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ? 16#ኢሳ. 53፥1። ነገር ግን ሁሉም የወንጌልን ትምህርት የሰሙ አይደለም፤ ኢሳይያስም፥ “አቤቱ፥ ምስክርነታችንንስ ማን አመነ? የእግዚአብሔርስ ክንዱ ለማን ተገለጠ?”#“የእግዚአብሔርስ ክንዱ ለማን ተገለጠ” የሚለው በግሪኩ የለም። ብሎአልና። 17ማመን ከመስማት ነው፤ መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው። 18#መዝ. 18፥4። ነገር ግን እንዲህ እላለሁ፤ በውኑ እስራኤል ብቻ አልሰሙምን? መጽሐፍ “ነገራቸው በምድር ሁሉ ተሰማ፤ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ደረሰ” ብሎ የለምን? 19#ዘዳ. 32፥21። እስራኤል ብቻ አልሰሙምን? ሙሴስ አስቀድሞ እንዲህ ብሎአቸው የለምን? “እኔ በማያስተውሉ ወገኖች አስቀናቸዋለሁ፤ ወገን ባልሆነውም አስቈጣቸዋለሁ።” 20#ኢሳ. 65፥1። ኢሳይያስም ደፍሮ፥ “ለአልፈለጉኝ ተገኘሁ፤ ለአልጠየቁኝም ተገለጥሁላቸው” ብሏል። 21#ኢሳ. 65፥2። ለእስራኤል ግን “ሁልጊዜ ከዳተኞችና ወንጀለኞች ወደሆኑት ሕዝብ እጄን ዘረጋሁ” ብሎአል።
Currently Selected:
ወደ ሮሜ ሰዎች 10: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ